ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጉዱሩ ወረዳ ውስጥ ባለፈው ሰኞ ተካሄደ በተባለ የድሮን ጥቃት “ስምንት ሰዎች ተገድለዋል” ሲል የኦሮሞ ነፃነት ግንባር መግለጫ አውጥቷል።
በሌላ በኩል እዚያው ዞን የአሙሩ ወረዳ ከተማ ኦቦራ ውስጥ ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ አምስት ፀጥታ አስከባሪዎች በታጣቂዎች እንደተገደሉ ከንቲባዋ ገልፀዋል።
“መንግሥት አካሂዶታል” የተባለው የሰኞው የድሮን ጥቃት የተፈፀመው በበሮ ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስትያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ካለ የበቆሎ ማሳ ላይ የደረሰውን ቡቃያ በመሰብሰብ ላይ እንደነበሩ ነው” ሲሉ አንድ ለደኅንነታቸው እንደሚሰጉ በመግለፅ ስማቸውን እንዳንጠራ የጠየቁ የአካባቢው ነዋሪ ተናግረዋል።
"የቤተ ክርስትያኑ የሆነ በቆሎ ሲሸለቅቁ ነበር 8 ሰዎች በድሮን ተመተው የሞቱት፤ አራት ሰዎች ደግሞ ቆስለው ኮምቦልቻ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ጉዱሩ ሆስፒታል እየታከሙ ነው" ብለዋል ነዋሪው።
ስለሁኔታው ለማጣራት የዚህ ዘገባ አጠናቃሪ ወደ ኮምቦልቻ ሆስፒታል ቢደውልም መረጃ ማግኘት አልቻለም። በአካባቢው በመንግሥት ኃይሎችና በኦሮሞ ነፃነት ጦር ሸማቂዎች መካከል የሚደረገው ግጭት በኅብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ መቀጠሉን ነዋሪው ተናግረዋል።
"እዚህ አካባቢ ጦርነት በተደጋጋሚ ነው የሚከሰተው። የመንግሥት ወታደሮችም፣ ጫካ ያሉ ታጣቂዎችም በዚህ ስለሚያልፉ ህዝቡ ላይ በርካታ ጉዳት ይደርሳል። እንዲህ በጅምላ ባይሆንም በየሣምንቱ ቢያንስ አንድ ሁለት ሰው ይሞታል። አንዳንዴ ጫካ ያሉ ታጣቂዎች የመንግሥት ኃይሎችም በድሮን የሚሞቱበት ጊዜ አለ። ይሄን ችግር በውይይት ካልሆነ በውግያ መፍታት አይቻልም" ብለዋል ለቪኦኤ በሰጡት ቃል።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር /ኦነግ/ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ “በጉዱሩ ወረዳ ልዩ ስሙ በሮ በተባለ ሥፍራ በብልፅግና የድሮን ጥቃት ታኅሳስ 15 አመሻሽ ላይ ስምንት ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል” ብሎ ሌሎች ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውንም በፅሁፍ አስፍሯል።
ድርጊቱን እንደሚያወግዝ የገለፀው ኦነግ ህዝቡ፣ ዓለምአቀፍ ማኅበረሰብና የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ግፊት እንዲያደርጉ አሳስቧል።
ጥቃቱን የፈፀመው “መንግሥት ነው” መባሉን የመንግሥቱ ቃል አቀባይ ለገሠ ቱሉ በብርቱ አስተባብለው ውንጀላውን “ፍፁም ቅጥፈት” ማለታቸውን ሮይተርስ ማምሻውን ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም ስለጥቃቱ ጥቆማዎች እንደደረሱትና እያጣራ መሆኑን የኮሚሽኑ የአካባቢው ፅህፈት ቤት ኃላፊ እንደነገሩት ሮይተርስ አክሎ አመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚያው ዞን አሙሩ ወረዳ ኦቦራ ከተማ ውስጥ ከትናንት በስተያ ማክሰኞ ታጣቂዎች አምስት ፀጥታ አስከባሪዎችን መግደላቸውን የከተማዪቱ ከንቲባ አቶ ለሜሳ ታደሰ ገልፀዋል።
ኦቦራ ከተማ አሁን መረጋጋቷንና ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ መመለሷን ከንቲባው ተናግረዋል።
ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ፡፡
መድረክ / ፎረም