በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከፊል የምርጫ ውጤት ይፋ ሆነ


የገለልተኛ ብሄራዊ ምርጫ ኮሚሽን ሰራተኛ፣ ጎማ ውስጥ በሚገኝ የምርጫ ጣቢያ ድምፅ የሚሰጡ መራጮችን ሲያስተናግድ - ታህሳስ 21፣ 2023
የገለልተኛ ብሄራዊ ምርጫ ኮሚሽን ሰራተኛ፣ ጎማ ውስጥ በሚገኝ የምርጫ ጣቢያ ድምፅ የሚሰጡ መራጮችን ሲያስተናግድ - ታህሳስ 21፣ 2023

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ገለልተኛ ብሄራዊ ምርጫ ኮሚሽን፣ አርብ እለት የተካሄደውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከፊል ውጤት፣ ይፋ አድርጓል።

በመጀመሪያ ዙር ይፋ የተደረገው በደቡብ አፍሪካ፣ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በካናዳ፣ በቤልጂየም እና በፈረንሳይ የሚኖሩ የኮንጎ ዲያስፖራ ነዋሪዎች የሰጡት ድምፅ ውጤት ሲሆን፣ ለፕሬዝዳንት ፊሊክስ ቼሰኬዲ ያመዘነ እንደሆነ ተገልጿል።

አርብ እለት በተካሄደው ምርጫ ድምፅ ይሰጣሉ ተብለው ከተጠበቁት 11ሺህ የዲያስፖራ መራጮች ውስጥ 5ሺህ 300 ሰዎች ብቻ ድምፅ የሰጡ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 4ሺህ 294ቱ ወይም ወደ 81 ከመቶ የሚጠጉት ለፕሬዝዳንት ቼሰኬዲ ድምፅ ሰጥተዋል። 11 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ ለተቀናቃኙ ሞሲ ካቱምቢ ድምፅ መስጠታቸው ተገልጿል።

44 ሚሊየን የሀገር ውስጥ ነዋሪዎች የተሳተፉበት ምርጫ ውጤት ከመጪው ቅዳሜ ጀምሮ ይፋ እንደሚሆን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ተቃዋሚዎች እና ገለልተኛ ታዛቢዎች ምርጫው ትርምስ የበዛበት እና ተዓማኒነት የሚጎድለው ነው ሲሉ ያቀረቡትን ተቃውሞ፣ የብሄራዊ ምርጫ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር ዴኒስ ካዲማ አልተቀበሉትም። በምትኩ ተቋማቸው በተቻለው መጠን ተዓማኒነት ያለው፣ ግልፅ እና ሁሉን ያሳተፈ ምርጫ ማካሄዱን ገልፀዋል።

አንዳንድ ተቃዋሚዎች ግን ምርጫው ህገወጥ አሰራሮች የታዩበት እንደሆነ በመከራከር አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ እየጠየቁ ነው።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG