በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በደላንታ የሆስፒታሉ አምቡላንስ በከባድ መሣሪያ ሲቃጠል አምስት ሰዎች እንደተገደሉ ተገለጸ


በደላንታ የሆስፒታሉ አምቡላንስ በከባድ መሣሪያ ሲቃጠል አምስት ሰዎች እንደተገደሉ ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:50 0:00

በደላንታ የሆስፒታሉ አምቡላንስ በከባድ መሣሪያ ሲቃጠል አምስት ሰዎች እንደተገደሉ ተገለጸ

በዐማራ ክልል፣ በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ የወገል ጤና ከተማ መግቢያ ላይ፣ ትላንት ኀሙስ አመሻሹን በተተኮሰ ከባድ መሣሪያ አምስት ሰዎች እንደተገደሉ፣ የዐይን እማኞች ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

በጥቃቱ፣ የደላንታ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አምቡላንስ እንደተቃጠለ የገለጹት እማኞቹ፣ የአሽከርካሪውና የላብራቶሪ ቴክኒሻኑ ሕይወት እንዳለፈ፣ በውስጡ የነበሩት የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅም ክፉኛ እንደቆሰሉ አስረድተዋል። የተቀሩት ሦስት ሟቾች፣ በሰዓቱ በግንባታ ሥራ ላይ የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደኾኑ፣ እማኞቹ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ፣ በሰሜን ወሎ ዞን በላስታ እና ሐብሩ ወረዳዎች ላይ በተተኮሰ ከባድ መሣሪያ፣ በንጹሐን ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

በላስታ ወረዳ ጃሮ ገበያ በሚባለው ስፍራ ላይ፣ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ፣ ከረፋዱ 4፡00 ላይ ተተኮሰ የተባለው ከባድ መሣሪያ፣ ለበርካታ ንጹሐን ሞት ምክንያት እንደኾነ፣ አስተያየት ሰጭዎች ተናግረዋል፡፡

ከጉዳተኞቹ ውስጥ እናት እና ልጅ እንዳሉበት ያመለከቱት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ የገበያ ቀን መኾኑ ደግሞ ጉዳቱን አባብሶታል፤ ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ በዚኹ በሰሜን ወሎ ዞን፣ ባለፈው ኅዳር 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በሐብሩ ወረዳ ጋቲራ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በወደቀ የከባድ መሣሪያ ጥይት፣ ጸበል እየተጸበሉና ሃይማኖታዊ አገልግሎት እየሰጡ የነበሩ ምእመናንና አገልጋዮች፣ ከባድ እና ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ የገዳሙ አበ ምኔት ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል፡፡

የሰሜን ወሎ ዞን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን መምሪያ፣ አካባቢው በኮማንድ ፖስት ሥር ስለኾነ፣ ተፈጸሙ ስለተባሉት ጥቃቶች መምሪያው መግለጽ እንደማይችል ጠቅሶ፣ ኮማንድ ፖስቱ ግን ኹኔታውን ገምግሞ ወደፊት መግለጫ ሊሰጥ እንደሚችል አመልክቷል፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG