በ37ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ዘመን፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ የነበሩት ሄንሪ ኪሲንጀር፣ በ100 ዓመት ዕድሜአቸው፣ በኬኔቲከት ግዛት በሚገኘው መኖሪያ ቤታችው፣ ከዚኽ ዓለም በሞት እንደተለዩ፣ የአማካሪ ድርጅታቸው አስታውቋል። ለዕድሜ ባለጸጋው ዕውቅ ዲፕሎማት ሞት የተሰጠ ምክንያት የለም።
ኪሲንጀር ሥልጣን ከለቀቁሞ በኋላ፣ ሉላዊ ተጽእኗቸው የቀጠለ አንጋፋ ዲፕሎማት እና የፖለቲካ ሰው ነበሩ።
እ.አ.አ ግንቦት 27 ቀን 1923፣ በፉርት፣ ጀርመን ውስጥ የተወለዱት ኪሲንጀር፤ በ1938፣ በ15 ዓመታቸው፣ ከአይሁዳዊ ቤተሰባቸው ጋራ ናዚዎችን ሸሽተው አሜሪካ ገብተዋል።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት፣ የአሜሪካንን ጦር የተቀላቀሉት ኪሲንጀር፣ በኋላም በሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ተከታትለው በመምህርነትም አገልግለዋል።
ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰን፣ ኪሲንጀርን በጸጥታ አማካሪነት የሾሟቸው ሲኾን፣ ቆይቶም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነቱን ቦታ እንዲይዙ አድርገዋል። ይህም ኪሲንጀርን፣ ሁለቱንም ሹመቶች፣ በአንድ ጊዜ የያዙ የመጀመሪያው ሰው አድርጓቸዋል።
ፖለቲካን፣ ከግብረ ገባዊ መሠረቱ ይልቅ በተጨባጭ ሥራ እና ጥቅም ላይ ተመርኩዞ ሊተገብር በመቻሉ ላይ ማተኮር አለበት፤ በሚለው አሠራራቸው ተለይተው ይታወቁ ነበር፤ ኪሲንጀር።
ከቬትናም ጋራ የነበረው ጦርነት እንዲቆም ላደረጉት ጥረት፣ ከሰሜን ቬትናሙ ሌ ዳክ ቶ ጋር የኖቤል የሰላም ሽልማት ያገኙት ኪሲንጀር፣ እስከ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ድረስ ያሉትን ኹሉንም ፕሬዚዳንቶች አማክረዋል። ይኹንና፣ ጆ ባይደን ወደ ቢሯቸው ጋብዘዋቸው እንደማያውቁ ተነግሯል።
መድረክ / ፎረም