በጋዛ በእስራኤል እና በሀማስ መካከል አርብ የጀመረው የአራት ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት 14 እስራኤላዊያን ታጋቾች እና 42 የፍልስጤም እስረኞች ልውውጥ ዛሬ ቅዳሜ እንደሚደረግ የእስራኤል ባለስልጣናት ገልጸዋል።
እስራኤል፣ የፍልስጤም ተዋጊ ቡድን ፣ ካታር ፣ ግብጽ እና ዩናይትድ ስቴትስ በተሳተፉበት ንግግር ወቅት በተደረሰው ስምምነት መሰረት ፣ውጊያው በሚቆምባቸው ጊዜያት ውስጥ ፣ ሀማስ በትንሹ 50፣ እስራኤል ደግሞ 150 ፍልስጤማዊያን እስረኞችን ለመልቀቅ ተስማምተዋል ።
በተያያዘ ዜና ዛሬ ቅዳሜ ለንደን ውስጥ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይሳተፋበታል ተብሎ የሚጠበቀውን ለፍልስጤም ድጋፍ ለመስጠት ያለመውን ሰልፍ አስመልክቶ ከተማው ዝግጅቷን አጠናክራለች ። ለፍልስጤም አብሮነት የተሰናዳውን ሰልፍ አስመልክቶ ከ1500 በላይ ፖሊሶች የስራ ጥሪ ደርሷቸዋል። ሰልፈኞች ፓርክ ሌን ከተባለው የከተማዋ ስፍራ ኋይት ሆል ወደ ተሰኘው ሌላ ስፍራ በእግራቸው ለማዝገም ቀጠሮ ይዘዋል ።
ሀማስንም ሆነ ሌላ የታገደ የሽብርተኛ ድርጅትን መደገፍ፣ በእንግሊዝ ህግ የተከለከለ መሆኑን የሚያሳስበውን ጨምሮ ፣ ሰልፈኞች ስነ-ስርዓት እንዲያከብሩ የሚያሳስብ በራሪ ወረቀት ፣ ፖሊስ ለሰልፈኞች እንደሚያዳርስም ተነግሯል ።
ዕድሜያቸው ከ2 እስከ 85 ዓመት የሆናቸው 13 እስራኤላውያን ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ 24 ታጋቾች አርብ አመሻሽ ላይ መለቀቃቸው ይታወሳል ። በተጨማሪም ሀማስ 10 የታይላንድ ዜጎችን እና አንድ ፊሊፒናዊ ታጋች መልቀቁን የኳታር መንግስት አስታውቋል።
የእስራኤል መንግስት በበኩሉ 39 ፍልስጤማዊያን ታዳጊ ሴት እና ወንድ እስረኞችን ለቋል ።
እስራኤል ለአራት ቀናት እንደሚቆይ የተነገረው ውጊያ የማቆም ስምምነት ሀማስ 10 ተጨማሪ ታጋቾችን በፈታ ቁጥር በአንድ ቀን እንደሚራዘም ተናግራለች።
መድረክ / ፎረም