በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

መንግሥት ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋራ ያካሔደው ድርድር ያለስምምነት መጠናቀቁን አስታወቀ


ኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት፣ “ኦነግ ሸኔ” እያለ ከሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋራ፣ በታንዛኒያ - ዳሬ ሰላም በሁለት ዙር ያካሔደው ድርድር ያለስምምነት እንደተጠናቀቀ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን አስታወቁ።

አምባሳደር ሬድዋን፣ በኤክስ የቀድሞ ትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋራ የተደራደረው፣ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በቀጠሉ ግጭቶች ምክንያት እየደረሰ ያለውን ሰብአዊ ሥቃይ ለማስቆም በማሰብ እንደኾነ ገልጸዋል።

በሁለተኛ ዙር የተካሔደው የአሁኑ ድርድር ዋና ዓላማው፣ “ጥይቶችን ዝም ለማሰኘትና እየደረሰ ያለውን አሠቃቂ ጉዳት እና ውድመት ለማስቆም” እንደነበር ያመለከቱት አምባሳደር ሬድዋን፣ ለድርድሩ አለመሳካት፣ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን ተጠያቂ አድርገዋል።

“በሌላኛው ወገን ግትርነት ምክንያት፣ ንግግሩ ያለስምምነት ተጠናቋል፤” ያሉት አምባሳደር ሬድዋን፣ የታጣቂው ቡድን “ዕንቅፋት የኾነ አካሔድ እና ከእውነታው የራቁ ፍላጎቶች” ሲሉ በዝርዝር ያልገለጿቸውን ጉዳዮች፣ ለድርድሩ አለመሳካት ዋና ምክንያቶች እንደኾኑ አመልክተዋል።

የድርድሩን ያለስምምነት መጠናቀቅ በተመሳሳይ ማህበራዊ ድህረገፅ ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በበኩሉ፣ ለኦሮሞ ህዝብ እና ለመላው ሀገሪቱ ህዝቦች የተለየ እውነታን ጠብቆ ከፍተኛ አመራሩን በዚህ ውይይት ላይ እንዳሳተፈ አስታውቆ፣ "የኢትዮጵያ መንግስት ግን ሀገሪቱ ውስጥ የማይፈቱ ለሚመስሉ የፀጥታ እና የፖለቲካ ችግሮች መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ፣ ከሰራዊቱ አመራሮች ጋር ትብብር ለመፍጠር ብቻ ፍላጎት እንዳለው" አስታውቋል።

ለኢትዮጵያ ገለልተኛ ተቋማት እንደሚያስፈልጉ ያመለከተው የሰራዊቱ መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ወደሚፈለገው ውጤት ለመሄድ ሁኔታዎች ለማስተካከል ባለመቻሉ "ታሪካዊ እድል ጠፍቷል" ብሏል።

አምባሳደር ሬድዋን በመልዕክታቸው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ንግግሮቹን ያካሔደው፥ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ ግዛትን የማስጠበቅ መብት እና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አንድነትን መሠረት ባደረገ ማኅቀፍ ውስጥ እና ሕገ መንግሥታዊ ደንቦችን ባከበረ መልኩ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ “መንግሥት በእነዚኽ መርሖዎች ማኅቀፍ ውስጥ ኾኖ፣ በተቻለው መጠን ከኹኔታዎች ጋራ ለመስማማት እና ለመተባበር ሞክሯል፤” ብለዋል።

በተጨባጭ ጉዳዮች እና በአካሔድ ሥነ ሥርዐቶች ላይ፣ በጋራ የሚያስማሙ መፍትሔዎችን ለማግኘት እና ለሰላም ሲባል ስምምነት ላይ ለመድረስም፣ መንግሥታቸው ጥረት ማድረጉንም አክለው ገልጸዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG