ጋዛ ውስጥ በሚገኙ ትላልቅ ሆስፒታሎች የእስራኤል የአየር ድብደባ ከተካሄደ በኋላ በሰሜን ጋዛ የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካባቢውን በመልቀቅ እየሸሹ ነው፡፡
እስራኤል የፍልስጤም ሲቪሎችን ከጋዛ ለማስወጣት ሆን ብላ እነዚህን የህክምና ተቋማት እያጠቃች ነው የሚል ክስ አስነስቷል።
በዚህ ሳምንት ብቻ ከ80ሺ በላይ ፍልስጤማውያን ጋዛን ለቀው መሰደዳቸው ተመልክቷል፡፡
ሆስፒታሎቹ ደህንነትን ለሚሹ የብዙ ፍልስጤማውያን መጠለያ ቢሆኑም በድብደባዎቹ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማህበር ዳይሬክተር ማርዋን ጂላኒ ትናንት ዓርብ በሰጡት መግለጫ በሰሜን ጋዛ ውስጥ አል-ሺፋ፣ አል-አውዳ፣ አልቁድስ እና የኢንዶኔዥያ ሆስፒታልን ጨምሮ አራት ሆስፒታሎች በ24 ሰዓታት ውስጥ የአየር ጥቃት ኢላማ መደረጋቸውን አስታውቀዋል።
ጂላኒ ከ400 በላይ የታመሙና የቆሰሉ ታማሚዎች እንዲሁም 14,000 ተፈናቃዮች በሆስፔታሎቹ ተጠልለው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት በጋዛ በአማካይ አንድ ልጅ በየ10 ደቂቃው እንደሚገደል የሚያሳየው አኃዛዊ መረጃ አስደንጋጭ መሆኑን ገልጿል።
ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት የጋዛ ጤና ስርዓት በአስከፊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጾ ከ36 ሆስፒታሎች 18ቱ እንዲሁም ከመጀመሪያ ደረጃ ጤና ጣቢያዎች ሁለት ሶስተኛው አገልግሎት የማይሰጡ ናቸው ብሏል ።
በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር በእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ ከ11,000 በላይ ፍልስጤማውያን፣ በዋነኛነት ሴቶች እና ህጻናት መሞታቸውን አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩልም የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እኤአ ጥቅምት 7 በሐማስ የሽብር ጥቃት የሞቱትን ሰዎች ቁጥር ከ1,400 ወደ 1,200 ዝቅ አድርጎታል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ፍላጎት እንደሌላቸው ተናግረዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ትናንት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የተኩስ አቁም ጥሪ አቅርበዋል።
"እስራኤል ራሷን የመከላከል መብት እንዳላት እገነዘባለሁ" ያሉት ማክሮን "ነገር ግን ሰላማዊ ዜጎች በቦምብ እየተደበደቡ ነው “ጨቅላ ህጻናት አሉ፣ ወይዛዝርት አሉ፣ አረጋውያን በቦምብ ተደብድበው ተገድለዋል። ለዚያ ምንም ምክንያት እና ህጋዊ መሠረት የለም፣ ስለዚህ እስራኤል ተኩሱን እንድታቆም እናሳስባለን" ብለዋል።
የእስራኤል ጦር ባለስልጣናት ሐማስ በሆስፒታሎች ስር ባዘጋጃቸው ዋሻዎች የጦር መሣሪያ ይደብቃል፣ በጋዛ ትልቁ ሆስፒታል አል-ሺፋ ስር የማዘዣ ማእከል አቋቁሞ ህንፃዎቹን ወታደራዊ ኢላማ አድርጓል ሲሉም ይከሳሉ፡፡
የሐማስ እና የሆስፒታል ሠራተኞች ግን ክሱ መሰረተ ቢስ ነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
መድረክ / ፎረም