በኒውዮርክ የሲቪል ማጭበርበር ችሎት ትናንት ረቡዕ ፍርድ ቤት የቀረቡት የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የዶናልድ ትረምፕ ሴት ልጅ ኢቫንካ ትረምፕ፣ ግዙፉን የአባታቸውን የንግድ ተቋም (ኢምፓየር) አደጋ ላይ የጣለውን የሪል ስቴት ስምምነቶችን ዝርዝር መረጃ አላታውስም ሲሉ መስክረዋል።
ባለፈው ሳምንት ምስክርነታቸውን እንደሰጡት ልክ እንደ ወንድሞቻቸው ዶናልድ ትረምፕ እና ኤሪክ ትረምፕ ፣ ኢቫንካ ትረምፕም፣ አጠራጣሪ ከሆነውና ወሳኙን የፍርድ ሂደት የሚመለከቱ ዳኛ ማጭበርበር ተፈጽሟል ካሉበት የግምገማ ዘዴ፣ ራሳቸውን ማራቅ የፈለጉ መምሰላቸው ተነግሯል፡፡
የኒውዮርክ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሌቲሺያ ጀምስ ያቀረቡት ክስ ዶናልድ ትረምፕ በቀላሉ ብድር እና ኢንሹራንስ ለማግኘት የሀብት እሴታቸውን ከፍ አድርገዋል የሚል ነው፡፡
የዳኝነት ችሎቱ፣ በማሴር፣ በኢንሹራንስ ማጭበርበር እና በውሸት የንግድ ሰነዶች ማዘጋጀት በቀረቡት ውንጀላዎች ላይ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሏል፡፡
ጠቅላይ አቃቤ ህጓ ጄምስ ትራምፕ ፣ትራምፕ በኒውዮርክ ንግድ እንዳይሠሩ እገዳ እንዲጣልባቸውና ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ቅጣት እንዲወሰንባቸው እንደሚፈልጉ ተዘግቧል፡፡
የቀድሞው ፕሬዚደንት እና የሪፐብሊካን ፓርቲ የሚቀጥለው ዓመት፣ እ.አ.አ የ2024 ግንባር ቀደም ተወዳዳሪ የሆኑት ትረምፕ ምንም አይነት ጥፋት አለመፈጸማቸውን እየተናገሩ ነው፡፡
መድረክ / ፎረም