በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ብሊንከን “አደገኛ” ያሉትን እየጨመረ የመጣ የሩሲያና ሰሜን ኮሪያ ትሥሥር አወገዙ


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሴኡል በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ንግግር ሲያደርጉ - ህዳር 9፣ 2023
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሴኡል በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ንግግር ሲያደርጉ - ህዳር 9፣ 2023

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን “አደገኛ እና እያደገ ነው” ያሉትን በሰሜን ኮሪያ እና በሩሲያ መካከል ያለውን ወታደራዊ ትብብር በይፋ አውግዘዋል።

ብሊንከን ውግዘቱን ያቀረቡት ፒዮንግያንግ ለሞስኮ የዩክሬን ጦርነት ፣ የጦር መሣሪያዎችን እያቀረበች ነው የሚለውን ዘገባ ተከትሎ ነው፡፡

ብሊንከን ከደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፓርክ ጂን ጋር ከተገናኙ በኋላ በሴኡል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "ይህ ለሁለታችንም ሆነ ለሌሎች የዓለም ሀገራት በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው" ብለዋል።

የደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ የስለላ ድርጅት ሰሜን ኮሪያ ከነሐሴ ወር መጀመሪያ አንስቶ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የመድፍ ጥይቶችን ወደ ሞስኮ እንደላከች እንደሚያምን አመልክቷል፡፡

ይህም የሩሲያን ጦርነት ለሁለት ወራት ያህል ለሚገመት ጊዜ የሚደግፍ አቅርቦት ነው ሲልም ድርጅቱ አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ምንም እንኳ ችግሮች ሊኖሩበት ይችላሉ ቢባልም ሩሲያ ሰሜን ኮሪያን በሳተላይት ቴክኖሎጂ እንደምትረዳ ፍንጭ መስጠቷ ተመልክቷል፡፡

ሩሲያ የሰሜን ኮሪያን የኒውክሌር አቅምን የምታጠናክርበት ሁኔታም ሊኖር ይችላል የሚል ስጋት ማደሩም ተጠቁሟል።

በሩሲያና ሰሜን ኮሪያ መካከል ቀጣይ የመሣሪያ ልውውጦች መኖራቸውን የሳተላይት ምስሎች ቢጠቁሙም ሁለቱም ሀገራት የተባለውን ክስ ውድቅ አድርገዋል፡፡

ብሊንከን በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ሁኔታውን ለማቃለል የተጠናከረ ጥረቶች እንዳሉ በመጥቀስ እነዚህን ግብይቶች የመፍታት አጣዳፊነት ላይ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ብሊንከን ደቡብ ኮሪያን ጨምሮ ዩናይትድ ስቴትስ እና አጋሮቿ እነዚህን ወታደራዊ ልውውጦች በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የተቀናጀ እርምጃ ለመመከት ቁርጠኛ መሆናቸውን አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG