በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የትግራይ እና የዐማራ ክልሎች አከራካሪ ቦታዎች ጉዳይ በሕዝበ ውሳኔ እንደሚፈታ የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቀ


ፋይል - የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህወሃት በደቡብ አፍሪካ፣ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ሲፈራረሙ
ፋይል - የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህወሃት በደቡብ አፍሪካ፣ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ሲፈራረሙ

ባለፈው ሳምንት አንድ ዓመት ያስቆጠረውን የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት አስመልክቶ፣ የፌዴራሉ መንግሥት ባወጣው መግለጫ፣ ለሁለቱ ክልሎች አከራካሪ ቦታዎች እልባት ለመስጠት የታቀዱ መፍትሔዎችን ለመተግበር እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

የሰላም ስምምነት አንደኛ ዓመት ጋራ ተያይዞ፣ ፈራሚ አካላቱ፣ አንዳቸው ሌላቸውን በአፈጻጸም ጉድለት እየወቀሱ ይገኛሉ፡፡

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ አገልግሎት ዛሬ ሰኞ፣ ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫው እንዳስታወቀው፣ የፌዴራሉ መንግሥት እና ተቋማት፣ የፕሪቶርያውን ስምምነት ከሚጠበቀው በላይ እየፈጸሙ እንደሚገኙ ገልጾ፣ በአንጻሩ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የሰላም ስምምነቱን በተሟላ ኹኔታ እየፈጸመ አይደለም፤ ሲል፣ ወቅሷል፡፡

ስምምነቱን በአግባቡ ያልፈጸመው የፌዴራሉ መንግሥት እንደኾነ የጠቀሰው ህወሓት በምላሹ፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ በኩል መፈጸም ያለባቸው ጉዳዮች በሚገባ እንደተፈጸሙ አስታውቋል፡፡

የኮምዩኒኬሽንስ አገልግሎቱ በዛሬ መግለጫው፣ የስምምነቱ አንድ አካል የኾነውን ለአከራካሪ ቦታዎች፣ “ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጥና ሁሉንም ወገኖች ሊጠቅም የሚችል” ያለውን የመፍትሔ አቋም እንደያዘ አመልክቷል፡፡

በዚኽም መሠረት፣ “ክረምት ደርሶ የእርሻ ሥራ ከመጀመሩ በፊት፣ ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ፤ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች በመረጧቸው አካላት እንዲተዳደሩ፤ በመጨረሻም፣ ደረጃ በደረጃ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ አቅጣጫ ተቀምጧል፤” ሲል፣ በቅደም ተከተል ዘርዝሯል፡፡ “ይህንም ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፤” ያለው መንግሥት፣ ስለ እንቅስቃሴዎቹ ግን በግልጽ የጠቀሰው ነገር የለም፡፡

የአከራካሪ ቦታዎቹ ጉዳይ፣ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረት እልባት እንዲያገኝ፣ የፕሪቶርያው ስምምነት በአንቀጽ 10 ድንጋጌው አስፍሯል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ደግሞ፣ የክልሎችን ወሰን በሚመለከት ጥያቄ የተነሣ እንደኾን፣ በሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት እንደሚፈጸም፤ ክልሎቹ ካልተስማሙ ደግሞ፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ እንደሚያገኝ በአንቀጽ 48 ደንግጓል፡፡

የዛሬውን መግለጫ አስመልክቶ፣ ከመንግሥት ኮምዩንኬሽንስ አገልግሎት ማብራሪያ የጠየቅን ሲኾን፣ በመግለጫው ላይ ከተመለከተው ውጪ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት እንደማይፈልጉ፣ የመሥሪያ ቤቱ ባለሥልጣናት ገልጸዋል፡፡

የኮምዩኒኬሽን አገልግሎቱ በመግለጫው፣ “የፌዴራል መንግሥት ለፕሪቶርያው ስምምነት አተገባበር ከሚጠበቅበት በላይ ተጉዟል፤” ብሏል፡፡

በአንጻሩ፣ “በአንዳንድ ነገሮች ወደ ኋላ እየቀረ፣ ስምምነቱን በተሟላ ኹኔታ አልፈጸመም፤” ሲል፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን ወቅሷል፡፡

ከፌዴራል መንግሥቱ ጋራ የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት የተፈራረመው ህወሓት በበኩሉ፣ “ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ፣ በትግራይ በኩል እንዲፈጸሙ የተቀመጡት ጉዳዮች በሚገባ ተፈጽመዋል፤” ሲል የፌዴራል መንግሥቱን ወቀሳ አስተባብሏል፡፡

ይልቁንም፣ በፌዴራል መንግሥቱ በኩል፣ “ወሳኝ መሠረታዊ ጉዳዮች በአግባቡ አልተፈጸሙም፤” ያለው ህወሓት፣ “ወራሪዎች” ሲል የጠራቸው አካላት፣ “በኀይል ከያዟቸው የትግራይ መሬቶች መውጣት የነበረባቸው ቢኾንም፣ እስከ አሁን እንዲወጡ አልተደረገም፤” በማለት ተችቷል፡፡

ይኸው ተግባር፣ ከከባድ መሣሪያዎች መፍታት ጋራ በትይዩ መከናወን እንደነበረበት የጠቀሰው ህወሓት፣ ተፈጻሚ ባለመኾኑ ግን፣ የትግራይ ሕዝብ ሥቃይ እንዲራዘም ተደርጓል፤ ብሏል፡፡

ግጭትን በዘላቂነት የማቆም የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባለመኾኑ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የትግራይ ሕዝብ ተበታትኖ፣ ነጻ እንዳልወጣ የገለጸው የትግራይ ሕዝብ ደግሞ፣ የጥይት ድምፅ ባይሰማም ለጥፋት እንደተጋለጠ፣ ህወሓት አመልክቷል፡፡

አከራካሪ ቦታዎች በሕዝበ ውሳኔ መፍትሔ እንዲያገኙ አቅጣጫ እንደተቀመጠ በፌዴራሉ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ የተገለጸውን አስመልክቶ፣ ከዐማራ እና ከትግራይ ክልሎች መንግሥታት አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው ሊሳካልን አልቻለም፡፡

በሌላ በኩል፣ የፌዴራሉም ይኹን የትግራይ ክልል የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸማቸው ግልጽነት እንደሚጎድለው በመጥቀስ የሚተቹ አካላት፣ በዐማራ ክልል፣ በመንግሥት ኀይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሔደ ላለው ግጭት፣ ከዋና መግፍኤዎች አንዱ እንደኾነ ብዙዎች እንደሚገልጹ ይታወቃል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG