በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ብሊንከን በመካከለኛው ምሥራቅ ያደረጉት ጉብኝት ካለ ውጤት ተጠናቀቀ


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር አንተኒ ብሊንከን ከባግዳድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ከመነሳታቸው በፊት ከኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሺያ አል-ሱዳኒ ጋር ስለነበራቸው ቆይታ ገለፃ ሲያደርጉ
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር አንተኒ ብሊንከን ከባግዳድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ከመነሳታቸው በፊት ከኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሺያ አል-ሱዳኒ ጋር ስለነበራቸው ቆይታ ገለፃ ሲያደርጉ

እስራኤል በሐማስ ላይ ጥቃቷን ባጠናከረችበት በዚህ ወቅት፣ በጋዛ የሚገኙ ሲቪሎች የሚረዱበትን መንገድ በተመለከተ በአካባቢው ሀገራት መካከል አንዳች ዓይነት መግባባት ለመፍጠር በመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝት ሲያደርጉ የቆዩት የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተንኒ ብሊንከን፣ የተሳካ ውጤት ሳያገኙ ቀርተዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ወደ አምስት የአካባቢው ሀገራት የተጓዙት ብሊንከን፣ ዛሬ ቱርክ ላይ ከሀገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን ጋር መክረዋል።

በሐማስ የታገቱ ሰዎችን ለማስለቀቅ እና ጦርነቱ ወደ ቀጠናው እንዳይስፋፋ፣ እንዲሁም በጋዛ የሚገኙ ሲቪሎች ስቃያቸው ጋብ እንዲል፣ እስራኤል እያካሄደች ካለው የማያባራ ጥቃት “ሰብዓዊ እፎይታ” እንድታደርግ በሚል በፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር ለቀረበው ሐሳብ ድጋፍ ለማሰባሰብ ብሊንከን ወደ ቀጠናው ሀገራት አምርተው የነበረ ቢሆንም፣ የተፈለገውን ውጤት እንዳላገኙ የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።

በእስራኤል እና በእስራኤል በተያዘችው ዌስት ባንክ፣ ዮርዳኖስ፣ ቆጵሮስ፣ ኢራቅ እና በስተመጨረሻም ዛሬ ቱርክ የነበሩት ብሊንከን፣ አንካራን ከመልቀቃቸው በፊት ሲናገሩ፣ “በሁሉም ነገር መግባባት እንደማንችል ግልጽ ነው፣ ነገር ግን በአንዳንድ ሁኔታዎች ላይ የጋራ እይታ አለ” ሲሉ ተደምጠዋል።

ብሊንከን ጉብኝታቸውን ያደረጉት፣ የእስራኤል ጦር የጋዛ ከተማን ከቦ፣ ሰሜናዊውንና በሐማስ ቁጥጥር ሥር ያለውን የሰርጥ ክፍል ተቆርጦ እንዲቀር ባደረገበት ወቅት ነው።

የእስራኤል ወታደሮች ዛሬ ሰኞ ወይም ነገ ወደ ጋዛ ከተማ እንደሚገቡ ሲጠበቅ፣ ከሐማስ ታጣቂዎች ጋር የመንገድ ላይ እንዲሁም በመሬት ውስጥ መተላለፊያ የሚደረግ ውጊያ ይጠብቃቸዋል ተብሏል።

እስከ አሁን 9ሺሕ 700 ፍልስጤማውያን እንደተገደሉ ሲነገር፣ በመጪዎቹ ቀናት፣ በሁለቱም ወገን የተጎጂዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተገምቷል።

በተቻለ መጠን ሲቪሎች እንዳይጎዱ እና ተጨማሪ የሰብዓዊ ርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ ለእስራኤል መናገራቸውን ብሊንከን አስታውቀዋል።

ብሊንከን ከቱርክ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን ጋር በሚነጋገሩበት ወቅት፣ በሚኒስቴር መ/ቤቱ አቅራቢያ የፍልስጤምን እና የቱርክን ባንዲራ የያዙ ተቃዋሚዎች ሰልፍ አድርገዋል። ሰልፈኞቹ ብሊንከን ቱርክን ለቀው እንዲወጡ ጠይቀዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG