በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኳታር መሪነት በእስራኤል እና ሐማስ መካከል የሚካሄደው ድርድር መቀጠሉ ተገለፀ


እስራኤል በምታካሂደው የአየር ድብደባ የጋዛ ሰርጥን እሳትና ጭስ ሸፍኗት ይታያል - ጥቅምት 17፣ 2016
እስራኤል በምታካሂደው የአየር ድብደባ የጋዛ ሰርጥን እሳትና ጭስ ሸፍኗት ይታያል - ጥቅምት 17፣ 2016

እስራኤል በከበባ ውስጥ በምትገኘው ጋዛ ላይ የምታካሂደውን ጥቃት አጠናቅራ በቀጠለችበት ወቅት፣ ጦርነቱን ለማስቆም በኳታር አሸማጋይነት በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የሚካሄደው ድርድር ቅዳሜ እለትም መቀጠሉን አንድ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጭ አስታወቁ።

ንግግሮች አልተቋረጡም ያሉት፣ ጉዳዩ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው በመሆኑ ማንነታቸው እንዳይገለፅ የጠየቁት ምንጭ፣ ሆኖም ጥቃቱ አርብ ምሽት ተጠናቅሮ ከመቀጠሉ በፊት ይካሄድ ከነበረበት ፍጥነት "እጅግ በቀዘቀዘ ሁኔታ" መቀጠሉን አመልክተዋል።

የእስራኤል የጦር ጀቶች በሐማስ በሚመራው የፍልስጤም ጋዛት ላይ ተጨማሪ ቦምቦችን ማዝነባቸውን በቀጠሉበት እና ወታደራዊ ኃላፊዎች ለረጅም ጊዜ ሲያስፈራሩት የቆዩትን የመሬት ላይ ጥቃት መጀመራቸውን ባስታወቁበት ወቅት፣ በከበባ ውስጥ የሚገኙት የጋዛ ነዋሪዎች ከውጪው ዓለም ጋር መገናኘት አልቻሉም።

ኳታር ላለፉስት ሦስት ሳምንታት ከጀርባ ሆና የሐማስን ባለስልጣናት እና እስራኤልን በማነጋገር ሰላም እንዲወርድ እና ታጋቾች እንዲለቀሱ ለማድረግ የዲፕሎማሲ ስራ ስትሰራ መቆየቷ ይታወሳል። በዚህ የማሸማገል ጥረቷም ባለፈው ሳምንት ሁለት አሜሪካዊ እናት እና ልጅ እንዲሁም ሁለት አረጋውያን እስራኤላዊ ሴት ታጋቾች ተለቀዋል።

እስራኤል እስላማዊው ቡድን ባደረሰው ጥቃት 1ሺህ 400 ዜጎቿ መገደላቸውን እና 25 የተለያዩ ሀገራት ዜግነት ያላቸውን ጨምሮ 224 ሰዎች ደግሞ ታግተው መወሰዳቸውን አስታውቃለች። እስራኤል ላለፉት ሦስት ሳምንታት በጋዛ ላይ ባካሄደችው ከመቼውም በላይ የጠነከረ የቦምብ ጥቃትም ከ7ሺህ በላይ በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የፍልስጤም የጤና ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

ከፍተኛ ሀብት እና መዋዕለ ንዋይ የማፍሰስ አቅም ያላት ትንሿ ኳታር፣ የፖለቲካ ቢሮው በዋና ከተማዋ ዶሃ ከሚገኘው ሐማስ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላት ሲሆን፣ ቀደም ሲልም በእስላማዊው ቡድን እና በእስራኤል መካከል ሰላም እንዲወርድ ከፍተኛ እገዛ አድርጋ ነበር።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG