በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ህወሓት ለዛሬ በጠራው የካድሬ ስብሰባ ባጸደቀው አጀንዳ ላይ ነገ ይወያያል ተባለ (የታደሰ)


መቐለ ከተማ የሚገኘው ሰማዕታት ሓወልት አዳራሽ፣ ጥቅምት 17 2016 ዓ.ም
መቐለ ከተማ የሚገኘው ሰማዕታት ሓወልት አዳራሽ፣ ጥቅምት 17 2016 ዓ.ም

- ጊዜያዊ አስተዳደሩ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፤ ከፓርቲው አመራሮች እና የፀጥታ ሓላፊዎች ጋራ ባደረጉት ውይይት ስብሰባው እንዲቆም መስማማታቸው ገልጿል።

ህወሓት፣ በመቐለ ከተማ፣ ለዛሬ ቅዳሜ የጠራውና እንዳይካሔድ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ማሳሰቢያ የተሰጠበት የካድሬዎች ስብሰባ፣ በዋና አጀንዳ ላይ ለመነጋገር፣ ለነገ እሑድ እንደተላለፈ ምንጮች ገለጹ።

በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሰው ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት)፣ በመቐለ የሰማዕታት ሓውልት አዳራሽ ለማካሔድ ባቀደው የሁለት ቀናት የካድሬዎች ስብሰባ አካሔድና የተሳታፊዎች ዝርዝር ላይ፣ ዛሬ ውይይት እንደተደረገበት፣ በስብሰባው ላይ የተገኙ ምንጮች ገልጸውልናል።

ስማቸውን እንዲጠቀስና ድምፃቸውም እንዳይሰማ የጠየቁ አንድ ተሳታፊ፣ ስብሰባው፣ በሰማዕታት ሓወልት አዳራሽ፣ ከቀትር በኋላ በ9፡00 እንደሚጀምር እንደተገለጸላቸው ነግረውኛል። ይኹንና፣ በተባለው ሰዓት ወደ አዳራሹ ባመራም፣ ከተሳታፊዎች በቀር መግባት እንደማይቻል ስለተነገረኝ፣ ወደ ውስጥ ዘልቄ ኹኔታውን ለመታዘብ አልቻልኹም።

ከቆይታ በኋላ ከስብሰባው ሲወጡ ካገኘኋቸው አንድ ተሳታፊ ባገኘኹት መረጃ፣ ስብሰባው ሕገ ወጥ እንደኾነና መካሔድ እንደሌለበት፣ ትላንት ማሳሰቢያ የሰጡት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት እና የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ እንዳልተገኙ አረጋግጫለኹ፡፡

እኚኹ ተሳታፊ፣ ስብሰባውን የፓርቲው ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል እንደመሩትና ከ600 በላይ ተሳታፊዎች እንደተገኙበት ነግረውኛል፡፡ በውይይቱ መጨረሻ፣ “በፓርቲው ላይ ያጠላው አደጋ ምንድን ነው?” የሚለው በዋና የመነጋገሪያ አጀንዳነት እንደተቀረጸ የገለጹልኝ ተሳታፊው፣ ይህም፣ ነገ እሑድ ውይይት እንዲደረግበት ከስምምነት ላይ እንደተደረሰበት ነግረውኛል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፣ ዛሬ ጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀትር በፊት የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች ከፓርቲው እና ፀጥታ ሓላፊዎች ጋራ ባደረጉት ውይይት ስብሰባው እንዲቆም መስማማታቸው ገልጿል። መግለጫው አክሎም "ለስብሰባ ወደ መቐለ ከተማ የገቡ የመንግሥት አመራሮችአስተዳደሩ ወደ አቀደው እህል የመሰብሰብ፣ አንበጣ የመከላከል እና በመስኖ ዝግጅት ሥራ ላይ እንዲሰማሩ መግባባት ላይ ተደርሷል" ብሏል::

"ይህን ውሳኔም ስብሰባውን ልጠሩት የፓርቲው አመራሮች ለስብሰባ የተገኙትን ካድሬዎች ማብራርያ ሰጥቶ እንዲበትናቸው አቅጣጫ ተቀምጧል" ሲል መግለጫም አስታውቋል::

ከዚህ ውጭ በክልል ደረጃ በመቐለ ከተማ የሚካሄድ ስብሰባ የለም ብሏል ጊዜያዊ አስተዳደሩ::

ይኸው የህወሓት ካድሬዎች ስብሰባ፣ የትግራይ ሕዝብ ካለበት ችግር ለመውጣት የሚያደርገውን ጥረት የሚያውክ ተግባር እንደኾነ በትላንት መግለጫቸው ላይ ያመለከቱት፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ “ሊገታ ይገባል” ሲሉም አሳስበዋል፡፡ የጊዜያዊ መንግሥቱን ሥራ በሚያደናቀፉትም ላይ፣ አስተዳደራቸው አስቸኳይ ርምጃ እንደሚወስድ፣ ፕሬዚዳንቱ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።

ህወሓት፣ የፓርቲ ሕጋዊ ሰውነቱ ዳግም እንደማይመለስለት፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተወስኖ ድርጅታዊ ህልውናው ቢሰረዝም፣ ውሳኔውን በመቃወም በእንቅስቃሴው እንደሚቀጥል ማስታወቁን፣ ከዚኽ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል።

በጉዳዩ ላይ፣ ከፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ በአካል እና በስልክ ተጨማሪ መረጃ እና ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግኹት ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ይከታተሉ።

ህወሓት ለዛሬ በጠራው የካድሬ ስብሰባ ባጸደቀው አጀንዳ ላይ ነገ ይወያያል ተባለ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:09 0:00

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG