የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ዜጎችን በአፈናቀሉና ልዩ ልዩ ጉዳቶችን በአደረሱ አካላት ላይ ተጠያቂነት ባለማስፈኑ፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ፍትሕ የማግኘት መብት እንደተፈነጋቸው፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርቱ አስታወቀ፡፡
የተቋሙ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፣ በዓመታዊ ሪፖርቱ ዙሪያ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ማብራሪያ፣ መንግሥት፥ በተፈናቃዮች ላይ በደል የፈጸሙ አካላትን ለሕግ ባለማቅረብና አስተማሪ ርምጃ ባለመውሰድ ብቻ ሳይኾን፣ ለተፈናቃዮች ተገቢውን ጥበቃ እና ድጋፍ ባለማድረግ ሐላፊነቱን እንዳልተወጣ ጠቅሰው ወቅሰዋል፡፡ በዚኽም የተነሳ ተጨማሪ መፈናቀል እየቀጠለ እንደኾነ፣ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ አመልክተዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡን “የሕግ ባለሞያዎች ለሰብአዊ መብቶች” የተሰኘ ሀገር በቀል የመብቶች ተሟጋች ድርጅት ዋና ዲሬክተር አቶ አምኃ መኰንን፣ መንግሥት ተጠያቂነትን ማስፈን ያልቻለው፣ በዐቅም እና በቁርጠኝነት ማነስ ሊኾን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ፣ ከሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አስተያየት እና ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለዛሬ አልተሳካም፡፡
ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ፡፡
መድረክ / ፎረም