ዚምባብዌ፣ ወደ 40 የሚደርሱ ልዩ ልዩ ማዕድናት እና ከዓለም ከፍተኛው የአልማዝ ክምችት ቢኖራትም፣ አብዛኛው የዚምባብዌ ሕዝብ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ይኖራል።
ማራንጌ፣ በዓለም ላይ ትልቁ የአልማዝ ክምችት የሚገኝበት የዚምባብዌ ገላጣ ሜዳ ነው። እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ዕንቊዎች፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዚኽ ስፍራ የወጡትም፣ እ.አ.አ በ2006 ዓ.ም. ነው።
መንግሥት በባለቤትነት የሚያስተዳድረው የዚምባብዌ የአልማዝ ኩባንያ፣ ሁሉም የዚምባብዌ ዜጎች ከማዕድን ቁፋሮው ተጠቃሚ እንዲኾኑ፣ ምርቱን ለማሳደግ እየጣረ እንደሚገኝ፣ የተቋሙ ቃል አቀባይ ሹገር ቻጎንዳ ይናገራሉ።
“ይህን እያደረግን ያለነው፥ የኅብረተሰብ ልማት ተቋማትን በመገንባት፣ የአካባቢውን ተወላጆች በመቅጠር፣ መሠረተ ልማት በመዘርጋት፣ የስፖርት እና የመዝናኛ ስፍራዎች የመሳሰሉ ምቹ ኹኔታዎች መሟላታቸውን በማረጋገጥ ነው። እነዚኽን አገልግሎቶች፣ በአቅራቢያው ለሚገኙ አካባቢዎችም እያስፋፋን ነው፤” ይላሉ ቻጎንዳ።
እነዚኽ ጥቅሞች፣ ለአካባቢው ነዋሪዎች ገና እንዳልደረሱ ቻጎንዳ ይገልጻሉ፡፡ በማራንጌ ሜዳ ላይ ዕድሜውን በሙሉ የኖረው አርትዌል ሙሻንግዊድዛ ግን፣ በማዕድን ማውጫ ስፍራው ያለውን ተጨባጭ ችግር በመዘርዘር፣ “የሚያሳስበንም ይህ ነው፤” ይላል። እርሱ እንደሚለው፥ ወላጆች የትምህርት ቤት ክፍያ መክፈል ስላልቻሉ፣ ልጆች ከትምህርት ቤት ይቀራሉ።
በመኾኑም፣ በአልማዝ ማዕድኑ አቅራቢያ የሚኖሩ ሕፃናት፣ የትምህርት ቤት ክፍያ እንዲቀንስላቸው ወይም ክፍያው እንዲቀርላቸው ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያመለክታል፡፡ በዚኽም ልጆች፣ ከአልማዙ ተፈጥሯዊ ጸጋ ተጠቃሚ እንደሚኾኑ ተስፋውን ይገልጻል፤ የተሻለ የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንደሚኖራቸውም ያምናል።
የዚምባብዌ የአልማዝ ኩባንያ፣ የአካባቢውን ሕፃናት ትምህርት ለማሻሻል፣ የሳይንስ ቤተ ሙከራዎች ያሏቸውን ትምህርት ቤቶች መገንባት እንደጀመረ ይገልጻል። የአገሪቱ ዜጎች፣ ከአልማዝ ማዕድኑ የሚሹት በረከት ግን፣ በትምህርት ቤት ግንባታ ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ ኢኮኖሚውንም የተሻለ እንዲደግፍ ይፈልጋሉ።
ይኹንና፣ የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር ማዕከል ዲሬክተሩ ፋራይ ማጉዉ፥ የአልማዝ ዘርፉ፣ እጅግ ለከፋ እና ለተደራጀ ወንጀል እንደተጋለጠ ይገልጻሉ። “አልማዙ ወዴት እንደሚሔድ፣ እንዴት ከሀገር እንደሚወጣና ገቢው ለምን እንደሚውል የሚያውቁት መሪዎቹ ብቻ ናቸው፤” ይላሉ ማጉዉ፡፡ አያይዘውም፣ የአልማዝ ኢንዱስትሪውን አስመልክቶ፣ እንደ ዜጋ፣ ከማንኛውም መረጃ ተገልለናል፤ ሲሉ፣ በዘርፉ ያለው የግልጽነት ጉድለት ዋናው ችግር እንደኾነ ያስረዳሉ።
በዚምባብዌ የሠራተኛ እና ኢኮኖሚ ልማት ምርምር ተቋም ውስጥ፣ የምጣኔ ሀብት ባለሞያ የኾኑት ፕሮስፔር ቺታምባራ በበኩላቸው፣ መረጃውን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ፣ ዝምባቡዌ፣ ከፊል ኢኮኖሚዋን በአልማዝ ላይ የገነባችውን የቦትስዋናን ምሳሌ እንድትከተል ይመክራሉ፡፡ሁለተኛው ነገር፣ “የማዕድናቱ ተጠቃሚነት ነው፤” የሚሉት ቺታምባራ፣ ይኸውም፣በኢንዱስትሪው የዕሤት ሰንሰለት ውስጥ ባለው ሒደት ውስጥ እንዲረጋገጥ ይጠይቃሉ። ተራው ዜጋ ከነዚኽ ሀብቶች ተጠቃሚ እንዲኾን ለማረጋገጥ፣ “ይህ አስፈላጊ ነው፤” ሲሉም ያብራራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ዚምባብዌ፣ አውሮፓዊቷን ሀገር ሉክሰምበርግን የሚያክል የአልማዝ ክምችት ቢኖራትም፣ በዓለም አቀፍ የአልማዝ ምርት ሰባተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
መድረክ / ፎረም