በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በጋዛ ሆስፒታሎች ውስጥ ያለው ሁኔታ አስከፊ መሆኑን አንድ ሐኪም ለቪኦኤ በላኩት የድምፅ መልዕክት አስታወቁ


 ትውልደ ፍልስጤማዊው እንግሊዛዊ እና የቀዶ ጥገና ሐኪሙ ዶ/ር ጋሳን አቡ-ሲታ
ትውልደ ፍልስጤማዊው እንግሊዛዊ እና የቀዶ ጥገና ሐኪሙ ዶ/ር ጋሳን አቡ-ሲታ

በጋዛ ሆስፒታሎች ውስጥ የሚታየው ሁኔታ እጅግ አስከፊ መሆኑን እና በግዜው መፍትሄ ካላገኘ ከፍተኛ የማኅበረሰብ ጤና ቀውስ ሊከተል እንደሚችል አንድ የድንበር የለሽ ሐኪሞች አባል ለቪኦኤ በላኩት የድምፅ መልዕክት አስታውቀዋል።

በጋዛ ሺፍታ በተባለ ሆስፒታል ውስጥ እንደሚሠሩ የገለጹት፣ ትውልደ ፍልስጤማዊው እንግሊዛዊ እና የቀዶ ጥገና ሐኪሙ ዶ/ር ጋሳን አቡ-ሲታ በላኩት የድምፅ መልዕክት እንዳሉት፣ በአሥር ሺሕ ባይሆን እንኳ፣ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ከእስራኤል በኩል ከሚመጣው ድብደባ ራሳቸውን ለማዳን በሆስፒታል ተጠልለው ይገኛሉ።

በሆስፒታሉ ግቢ፣ በሆስፒታሉ ውስጥ በሚገኙ ደረጃዎች፣ መተላለፊያዎች፣ እንዲሆም በሆስፒታል አልጋዎች መካከል ባለው ቦታ ሳይቀር ተጠልለው እንደሚገኙ ሐኪሙ ተናግረዋል።

በሆስፒታሉ የውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ፣ የንጽህና ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ ነው ሲሉ ዶ/ር ጋሳን ተናግረዋል።

“ሰዎች በቦምብ ጥቃቱ ምክንያት ፍራቻ ውስጥ ይገኛሉ። ፍርሃታቸውም ምክንያታዊ ነው” ብለዋል ሐኪሙ፡፡

“ዛሬ ቤተሰቡን ሊያይ የሄደ የቀዶ ጥገና ሐኪም፣ ከ30 የቤተሠብ አባላቱ ጋር በጥቃቱ ሕይወቱን አጥቷል” ብለዋል ሐኪሙ ዶ/ር ጋሳን አቡ-ሲታ። የሃኪሙ ስም ሚድሃት ሳኢዳም እንደሚባል እና ከሆስፒታል ሠራተኞች ውስጥ ሕይወቱ በጥቃቱ ያለፈ እርሱ ብቻ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ወደ ሆስፒታል ለመምጣት የደህንነቱ ሁኔታ አስፈሪ በመሆኑ እና አንዳንዶቹ ሠራተኞች ከቤተሠባቸው ጋር ለመሆን በመወሰናቸው ምክንያት፣ የሆስፒታል ሠራተኞች ቁጥር የተመናመን መሆኑን ሐኪሙ ጠቁመዋል። አንዳንዶቹ የቤተሰብ አባላት ስለሞቱባቸው፣ ሌሎች ደግሞ በመገደላቸው የሠራተኛው ቁጥር ተመናምኗል ብለዋል።

እስራኤላውያኑ፣ በተለይም በሰሜን ጋዛ ያሉ ሆስፒታሎችን ለማዘጋት ግፊት እያደረጉ መሆኑን፣ የሆስፒታል ሃላፊዎች ጋር በመደወል ሆስፒታሎቹን ኢላማ እንደሚያደርጉ በመዛት ላይ መሆናቸውን፣ በፍልስጤማውያን ላይ ጫና በመፍጠር የጤና ሥርዓቱ እንዲፈርስ ተጽእኖ በማሳደር ላይ እንደሆኑ ሐኪሙ ጨምረው ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት እርሳቸው በሚሠሩበት ሺፍታ ሆስፒታል 150 የሚሆኑ ታካሚዎች የቀዶ ጥገና እንደሚያስፍልጋቸው፣ ነገር ግን ያንን ማድረግ እንዳልቻሉ ዶ/ሩ ተናግረዋል።

በተገቢው ሰዓት ቀዶ ጥገና አለማድረግ የሚያስከትለውን ችግር እያስተዋሉ መሆኑንም አውስተዋል።

የሆስፒታል አቅርቦቶች እያለቁ መሆኑን እና የውሃ እና ምግብ አቅርቦት እጅግ አናሳ መሆኑን የተናገሩት የቀዶ ጥገና ሐኪሙ ዶ/ር ጋሳን አቡ-ሲታ፤ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ ማሕበረሰብ ጣልቃ ገብቶ፣ ለሆስፒታሎቹ አስፈላጊውን ለማድረስ መተላለፊያ እንዲከፈት ካላደረገ፣ ወይም ታካሚዎቹን ወደ ሌላ ሥፍራ ወስደው ማከም ካልቻሉ እንዲሁም የቦምቡ ጥቃት ካልቆመ፣ ነገሮች ወደ ፍጹም አስከፊ ሁኔታ እያመሩ እንደሆነ ለቪኦኤ በዋትስ አፕ መተግበሪያ በላኩት መልዕክት አስታውቀዋል።

///

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG