የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት የጋዛ ከተማ እና ሰሜናዊ አካባቢ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው ወደ ደቡብ መጓዛቸውን እንዲቀጥሉ በማሳሰብ የቀራቸው የስድስት ሰዓታት ጊዜ መሆኑን አስጠንቅቋል፡፡
ማስጠንቀቂያው የተሰጠው ሃማስ በጋዛ ከ120 በላይ ንፁሀን ዜጎችን አግቶ መያዙን የመከላከያ ሃይሉ ባረጋገጠበት ወቅት መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ሃማስ በበኩሉ ሲቪሎች የእስራኤልን መከላከያ ኃይሎች (IDF) የመልቀቂያ ጥሪ ችላ እንዲሉ መክሯል፣ ይህም ቀድሞውንም የነበረውን አስከፊ ሁኔታ አወሳስቦታል።
የጋዛ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር “በአሳዛኝ ሁኔታ አካባቢውን ለቀው እየተሰደዱ ባሉ ሰዎች ላይ እስራኤል ባደረገችው የአየር ድብደባ 70 ሰዎች ሲሞቱ ፣ 200 ሰዎች ቆስለዋል” ሲል ተናግሯል፡፡
በሌላ በኩል እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኘውን የሂዝቦላህ ዒላማ መምታቷን አስታውቃለች፡፡ በዚያ አካባቢ ያለውም ውጥረት ተባብሷል።
የተባበሩት መንግሥታት ጋዛ ውስጥ 423ሺ ሰዎች መፈናቀላቸውን ተናግሯል። እየተባባሰ ለመጣው ቀውስ ምላሽ ለመስጠት ሩሲያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የሰብአዊ ተኩስ ማቆምን የሚጠይቅ ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ አሰራጭታለች።
እኤአ ጥቅምት 7 በሃማስ ወረራ የጀመረው ግጭት ከሁለቱም ወገኖች ቢያንስ የ3,200 ሰዎች ህይወት ቀጥፏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በቅርቡ በሃማስ ጥቃት ለተጎዱ አሜሪካውያን ቤተሰቦች፣ ዜጎቹን በሰላም ወደ አገራቸው ለመመለስ ቁርጠኛ መሆናቸውን በግል አረጋግጠዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የዮርዳኖስን ንጉስ አብዱላህ እና የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስን ጨምሮ ከአካባቢው መሪዎች ጋር ተወያይተዋል።
መድረክ / ፎረም