በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በጋዛ ላይ የተጣለው ከበባ እንዲነሳ የተመድ ተቋማት ጠየቁ 


የሃይል ማመንጫ አካባቢ ጭስ ሲወጣ ይታያል፤ አሻከሎን፣ እስራኤል እአአ ጥቅምት 7/2023.
የሃይል ማመንጫ አካባቢ ጭስ ሲወጣ ይታያል፤ አሻከሎን፣ እስራኤል እአአ ጥቅምት 7/2023.

የነፍስ አድን ርዳታን መከልከል በዓለም አቀፉ ሰብአዊነት ሕግ ወንጀል መሆኑን በመግለፅ፣ እሥራኤል በጋዛ ላይ የጣለችውን ከበባ እና የአቅርቦቶች መቋረጥ እንድታነሳ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት ጠየቁ።

የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቃል አቀባይ ራቪና ሻምዳሳኒ ማክሰኞ እለት በጄኔቫ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "ለሲቪል ህዝብ ህልውና ወሳኝ የሆኑ አቅርቦቶች መገደብ የለባቸውም" ብለዋል።

"ሲቪሎች የተከበቡ አካባቢዎችን ጥለው መውጣት ከፈለጉ ሊፈቀድላቸው ይገባል። ማንኛውም ገደብ አስፈላጊ ከሆነ ወታደራዊ ምክንያት ሊኖረው ይገባል፣ አለበለዚያ ግን ጅምላ ቅጣት ይሆናል" ያሉት ሻምዳሳኒ፣ "ይህ ደግሞ በዓለም አቀፉ ሰብዓዊ ህግ በግልፅ የተከለከለ እና የጦር ወንጀል ሊሆን የሚችል ነው።"

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት (ኦቻ) በዕለታዊ ዘገባው ባወጣው መረጃ፣ እስራኤል ማክሰኞ እለትም በጋዛ ላይ የአየር ድብደባ መቀጠሏን እና ሮኬቶች ከጋዛ ወደ እሥራኤል መተኮሳቸውንም አስታውቋል። በሁለቱም በኩል የሟቾች ቁጥር መጨመሩንም አመልክቷል።

እስከ ሰኞ ምሽት፣ የውጭ ሀገር ዜጎችን ጨምሮ፣ 900 እሥራዔላውያን መሞታቸውን እሥራዔል ስታስታውቅ፣ በጋዛ የሚገኘው የጤና ሚኒስትር፣ ቢያንስ 687 ፍልስጤማውያን መሞታቸውን ይፋ አድርጓል።

ኦቻ በሪፖርቱ፣ በጋዛ የሚኖሩ 200 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው መፈናቀላቸውን አስታውቆ፣ አብዛኞቹ በመንግስታቱ ድርጅት ትምህርት ቤቶች ውስጥ መጠለላቸውን አስታውቋል።

የእስራኤል ባለሥልጣናት ለጋዛ ሰርጥ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚሰጠውን ብቸኛውን የኃይል ምንጭ ማቋረጣቸውን ያመለከቱት የኦቻ ቃል አቀባይ ጂንስ ላሬክ፣ በጋዛ "በጥቂት ቀናት ውስጥ ነዳጅ ሊያልቅ ይችላል" ብለዋል። እሥራኤል የውሃ አቅርቦት በማቋረጧም ከ610 ሺ በላይ ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱንም ገልጸዋል።

"ይህ ቀውስ ገና መጀመሩ ነው" ያሉት ላሬክ "ያለ መብራት፣ ያለ ኃይል እና ያለ ንፁህ ውሃ አቅርቦት የሚያልፍ እያንዳንዱ ሰዓት በሰዎች ጤና እና ምላሽ የመስጠት አቅም ላይ ከፍተኛ ስጋት ይፈጥራል" ሲሉ አክለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት፣ ከቅዳሜ አንስቶ በጋዛ ሰርጥ ውስጥ የሚገኙ የጤና ተቋማት እና ሰራተኞች ላይ 13 ጥቃቶች መድረሳቸውን አረጋግጧል። ስድስት የጤና ባለሙያዎች መገደላቸውን እና አራት መቁሰላቸውንም ገልጿል።

የጤና ተቋሙ ቃል አቀባይ የሆኑት ታሪክ ያሳሬቪች "በጋዛ ሰርጥ በሚገኙ ሰባት ዋና ሆስፒታሎች ውስጥ የነበሩት አቅርቦቶች በሙሉ ጥቅም ላይ ውለዋል" ያሉ ሲሆን፣ አስቸኳይ የሆኑ የጤና አቅርቦቶችን ከሀገር ውስጥ ገበያዎች ለመግዛት እና ወደ 500 ለሚደርሱ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ህክምና ለመስጠት፣ የዓለም ጤና ድርጅት 1 ሚሊዮን ዶላር በማዘጋጀት ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

አስፈላጊ አቅርቦቶችን ለሰዎች ለማድረስ ሰብአዊ መተላለፊያ ኮሪደር ያስፈልጋል ያሉት ቃል አቀባይ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በዚህ ዙሪያ እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

በመንግስታቱ ድርጅት ስር፣ ለፍልስጤም ስደተኞች የርዳታ እና ሥራዎች ማስተባበሪያ ተቋም፣ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት ታማራ አልሪፊ በበኩላቸው የእሥራኤል ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አመልክተዋል። ከዮርዳኖች ዋና ከተማ፣ አማን ሆነው መግለጫ የሰጡት አልሪፊ፣ "የአየር ጥቃቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ ለአይነ ስውራን የሚያገለግል ትምህርት ቤት እና የድርጅቱን ዋና መስሪያ ቤት ጨምሮ 18 ተቋማችን ላይ ጉዳት ደርሷል" ብለዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር የሚንቀሳቀሱ 80 ትምህርት ቤቶች፣ በመኖሪያ ቤታቸው ጥቃት ሊደስበት ወይም ሊወድም ይችላል ብለው የፈሩ ከ137 ሺህ በላይ የጋዛ ነዋሪዎችን ማስጠለሉንም ዳይሬክተሯ ገልጸዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው መፈናቀል ድርጅትታቸው ከሚችለው አቅም በላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በጋዛ ሰርጥ ከ2.2 ሚሊየን በላይ ሰዎች የሚኖሩ ሲሆን 1.7 ሚሊየን የሚሆኑት በተባበሩት ከመንግስታቱ ድርጅት የጤና፣ ትምህርት እና ምግብ እርዳታ የሚያገኙ ፍልስጤማዊ ስደተኞች ናቸው።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG