“ዓለም ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየተከፋፈለ፣ ይበልጥም እየተበታተነና ሁሉም ወደ ራሱ የሚያይ እየኾነ መጥቷል፤” ሲሉ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ ወቀሱ። “በ31 ሀገራት ውስጥ፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ታይቶ በማያውቅ ደረጃ፣ ቁጥራቸው አርባ አራት የሚደርሱ ዐዲስ የአስቸኳይ ጊዜ ኹኔታዎች እና የአስከፊ ጊዜ ቀውሶች ታሪክ ተመዝግበዋል፤” ሲሉ፣ የወቀሳቸውን ምክንያት አስረድተዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ከፍተኛ ኮሚሽነር፣ ትላንት ጄኒቫ ላይ፣ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መርሐ ግብር ላይ ባሰሙት በዚኽ ንግግራቸው፣ “የገጠመው የረድኤት ገንዘብ መራቆት፣ የገነነና መዘዙም የተረጂዎችን ዕጣ ለበረታ ፈተና የሚዳርግ፣ ስደተኞችን አስጠልለው የጎላውን ድጋፍ በመስጠት ላይ በሚገኙ ሀገራትም ላይ ከባድ ጫና የሚፈጥር ነው፤” ብለዋል።
ቀደም ሲል በባንግላዲሽ፣ በዮርዳኖስ እና በበርካታ የአፍሪቃ ሀገራት፣ አሳሳቢ በኾነ ደረጃ የርዳታ ምግብ አቅርቦት መጠን መቀነሱን፣ ኮሚሽነሩ አውስተዋል፡፡ ይህም፣ ከፍተኛ የጥበቃ አገልግሎቶች ከሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች አንዷ እንደኾነችው ምሥራቃዊ የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ያሉ አካባቢዎችን፣ “ወሳኙን አገልግሎት እንዲቀንሱ አስገድዷል፤” ሲሉ አስረድተዋል።
“ሁሉም ስደተኞች እና ፍልሰተኞች ወደ ባለጸጋ ሀገራት ነው የሚሔዱት” የሚለው እሳቤ፣ መሠረት የለሽ እንደኾነ በግልጽ እንዲታወቅ የጠየቁት ኮሚሽነሩ፣ ይልቁንም ብዙዎቹ፣ ሊጠለሉ ወደሚችሉበትና መጀመሪያ ወደገጠማቸው አገር እንደሚሔዱ፣ ግራንዲ ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም፣ ከስደተኞች 69 በመቶ የሚኾኑት፣ በአጎራባች ሀገራት ውስጥ እንደተጠለሉ በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡ ከቀዬአቸው በኃይል እንዲፈናቀሉ ከተደረጉት 90 በመቶዎቹ፣ “ከተጠለሉባቸው ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ውስጥ ነው የሚቀሩት” ሲሉም መከራከሪያቸውን አጠናክረዋል፡፡
መድረክ / ፎረም