በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሃማስን ጥቃት ተከትሎ ኔታንያሁ 'ጦርነት ላይ ነን' አሉ


የፖሊስ አባላት፣ በደቡብ እስራኤል ከጋዛ ሰርጥ በተተኮሰ ሮኬት ከተመታው ስፍራ፣ አንዲስት ሴት እና ልጇን ሲያወጡ - ጥቅምት 7፣ 2023
የፖሊስ አባላት፣ በደቡብ እስራኤል ከጋዛ ሰርጥ በተተኮሰ ሮኬት ከተመታው ስፍራ፣ አንዲስት ሴት እና ልጇን ሲያወጡ - ጥቅምት 7፣ 2023

እስራዔል የጋዛ ሰርጥን ከሚቆጣጠሩት የሃማስ ታጣቂዎች ጋር "ጦርነት ላይ ነች" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አስታወቁ።

የጋዛ ሰርጥን የሚያስተዳድሩት የሃማስ መሪዎች ቅዳሜ ረፋድ ላይ፣ በእስራኤል የተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ ጥቃት ከከፈቱ ወዲህ፣ ኔታንያሁ የመጀመሪያ መልዕክታቸውን በቴሌቭዥን ለህዝብ አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠባባቂ ወታደሮች እንዲጠሩ ያዘዙ ሲሆን፣ ሃማስ "እስካሁን ድረስ አይቶ የማያውቀውን ዋጋ ይከፍላል" ሲሉ ቃል ገብተዋል።

"ጦርነት ላይ ነን" ሲሉ አስረግጠው የተናገሩት ኔታንያሁ "ዘመቻ ወይም ከበባ እያካሄድን አይደለም፣ ጦርነት ላይ ነን" ብለዋል።

ኔታንያሁ አክለው፣ ጦራቸው በሃማስ ታጣቂዎች የተወረሩትን እና፣ ከእስራዔል ወታደሮች ጋር ውጊያ እየተካሄደባቸው የሚገኙትን ከተሞች እንዲያስለቅቁ አዘዋል።

ቅዳሜ ዕለት ሃማስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን በእስራዔል ላይ የተኮሰ ሲሆን በደርዘን የሚቆጠሩ ተዋጊዎች ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግባቸውን ድንበሮች አልፈው እንዲገቡ አድርጓል። ድርጊቱ እስራዔል በበዓል ቀን፣ ባልጠበቀችው ሁኔታ የተፈፀመ፣ ከፍተኛ የኃይል ወረራ መሆኑም ተገልጿል።

በጋዛ ድንበር ላይ ለሳምንታት ከዘለቀው ውጥረት በኋላ፣ ሃማስ ጥቃቱን እንዲከፍት ምን እንዳነሳሳው እስካሁን አልታወቀም። ሆኖም የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ መሪ የሆኑት መሃመድ ዲየፍ "አል-ቃሳ አውሎ ንፋስ" ሲሉ የጠሩትን ዘመቻ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

ዲየፍ በተቀረፀ ድምፅ ባስተላለፉት መልዕክት "ሲበቃ፣ ይበቃል" ያሉ ሲሆን፣ ከምስራቅ እየሩሳሌም እስከ ሰሜናዊ የእስራዔል ክፍል የሚገኙ ሁሉም ፍልስጤማውያን ትግሉን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አድርገዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG