በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኬቭን ማካርቲ ተነሱ (የታደሰ)


የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የምክር ቤቱ ህንፃ ዛሬ መስከረም 22/16 ዓ.ም ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ።
የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የምክር ቤቱ ህንፃ ዛሬ መስከረም 22/16 ዓ.ም ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ።

የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔውን አነሳ።

435 መቀመጫ ያለው ምክር ቤት ዛሬ ከቀትር በኋላ ለአርባ አምስት ደቂቃ ባካሄደው የድምፅ ሥነ ሥርዓት የአፈጉባዔው ቢሮና መቀመጫው ክፍት እንዲሆን የወሰነው 216 ለ210 በሆነ ድምፅ ሲሆን ዴሞክራቲክ እንደራሴዎች የአፈጉባዔውን መነሳት ደግፈዋል።

ኬቭን ማካርቲ ቦታቸውን ላለማጣት ከአምስት በላይ ሪፐብሊካን እንደራሴዎች መነሳታቸውን መደገፍ ያልነበረባቸው ቢሆንም ስምንቱ እንዲነሱ ደግፈው ድምፅ ሰጥተዋል።

ሥራ ላይ ያለ አፈጉባዔ በዚህ ሁኔታ በራሱ ፓርቲ እንደራሴዎች ከመንበሩ ሲነሳ በሃገሪቱ ታሪክ የዛሬው የመጀመሪያ ነው።

ማካርቲ ከስምንት ወራት በፊት ቦታውን የያዙት በራሳቸው ፓርቲ ውስጥ በተነሳ ውዝግብ ምክንያት ተቃውሞ ከበዛበት ከተራዘመና ለ15 ጊዜ ከተደጋገመ የድምፅ ሥርዓት በኋላ ነበር።

የአፈጉባዔውን መዶሻ ለመጨበጥ በፓርቲያቸው ውስጥ ከተቀናቃኞቻቸው ጋር ባደረጉት ድርድር ለዛሬው መነሳታቸው ቀላል መሠረት የጣለ ግዴታ ገብተው የነበረ ሲሆን እርምጃው በምክር ቤቱ ታሪክ እጅግ አቅመቢስ አፈጉባዔ ያደረጋቸው እንደነበር ሲነገር ቆይቷል።

ተከታዩ አፈጉባዔ ማን እንደሚሆንና እስከዚያም ምክር ቤቱ በማን እንደሚመራ የታወቀ ነገር የለም።

አፈጉባዔው እንዲነሱ የውሣኔ ሃሳብ ያቀረቡት የፍርሎሪዳ እንደራሴ ማት ጌትዝ ናቸው።

የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔው ኬቭን ማካርቲ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የምክር ቤቱ ህንፃ ዛሬ መስከረም 22/16 ዓ.ም ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ።
የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔው ኬቭን ማካርቲ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የምክር ቤቱ ህንፃ ዛሬ መስከረም 22/16 ዓ.ም ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ።

ጌትዝ የማካርቲ ቢሮና ቦታ ክፍት እንዲሆን ለኮንግረሱ ጥያቄ ያስገቡት የሃገሪቱን መንግሥት በከፊል ከመዘጋት ያዳነ የ45 ቀናት የበጀት ክፍተት ማሟያ ስምምነት ባለፈው ዓርብ፤ መስከረም 19 የበጀት ዓመቱ ያለገንዘብ ከመጠናቀቁ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ከዴሞክራቶቹ ጋር ከደረሱ ባኋላ ነበር።

ማካርቲ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ደጋፊዎች አንስተውት በነበረ ኮንግረሱን አደጋ ላይ የጣለ ወረራና ሁከት ላይ በተከታታይ በያዙት ትረምፕ ዘመም አቋም፣ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ላይ ኮንግረሱ የክስና የማስነሳት ምርመራ (ኢምፒችመንት ኢንኳየሪ) እንዲከፈት በማዘዛቸውና በዴሞክራቶቹ ሙሉ ድጋፍ የበጀት ክፍተት ማሟያ ድምፁ በተሰጠ ማግሥት ዴሞክራቶቹን መልሰው ጥፋተኛ አድርገው በመገናኛ ብዙኃን በመናገራቸው “የዛሬውን ዕለት ሊያስሾልኳቸው ይችሉ ነበር” እያሉ ተንታኞችና እራሳቸውም ዴሞክራቶቹ የሚናገሩላቸውን እንደራሴዎች ማስቆጣታቸው ተሰምቷል።

በህገመንግሥቱ መሠረት የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ ፕሬዚዳንቱ በአጋጣሚ ባይኖር ቦታውን ለመተካት ከምክትል ፕሬዚዳንቱ ቀጥሎ ያለ ሰው ነው።

ቀጣይ ሁኔታዎችንም እየተከታተልን እናሳውቃለን። በነገ ሥርጭቶቻችን የባለሙያዎችን ትንታኔዎች ይጠብቁ። ሃሳቦቻችሁን አንሸራሽሩ።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG