በሶማሌና በኦሮምያ አዋሳኝ አካባቢ ባቢሌ አቅራቢያ በሁለቱ ክልሎች ፀጥታ ኃይሎች መካከል የዛሬ ሁለት ሣምንት በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ ተፈናቃዮችና ነዋሪዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።
መስከረም 7 / 2016 ዓ.ም. በክልሎቹ የፀጥታ ኃይሎች መካከል በተነሳው የተኩስ ልውውጥ ወቅት ቆሎጂ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የነበሩ ቢያንስ ስድስት ተፈናቃዮች መገደላቸውንና ብዙ ሰው መቁሰሉን፤ በሌሎችም የአካባቢው ሲቪል ነዋሪዎች ላይ የህይወትና የአካል ጉዳት መድረሱን ኮሚሽኑ ገልጿል።
ተጎጂዎችን፣ የሁለቱንም ክልሎች የፀጥታ ጥበቃ አካላት፣ የቆሎጂ መጠለያ ሠራተኞችንና የሆስፒታል ባለሞያዎችን ማነጋገሩን ኢሰመኮ አመልክቶ ምርመራ እንዲካሄድና አጥፊዎች እንዲጠየቁ ጥሪ አድርጓል።
የተፈናቃዮች ጥበቃን በተመለከተ በተፈረመው የአፍሪካ ኅብረት የካምፓላ ስምምነት መሠረት የመንግሥት የፀጥታ አካላት የመጠለያ ጣቢያዎችን ደኅንነት ለአደጋ ሊያጋልጡ ከሚችሉ አድራጎቶች ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ኮሚሽኑ አሳስቧል።
መድረክ / ፎረም