በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የፍልሰተኞች ድርጅት ዐዲሷ ሓላፊ አፍሪካን ሊጎበኙ ነው


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት(IOM) ዐዲሷ ሓላፊ አሚ ፖፕ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት(IOM) ዐዲሷ ሓላፊ አሚ ፖፕ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት(IOM) ዐዲሷ ሓላፊ፣ በቅርቡ አፍሪካን እንደሚጎበኙ ታውቋል።

ትላንት እሑድ የድርጅቱን ሓላፊነት የተረከቡት አሜሪካዊቷ አሚ ፖፕ፣ በዐዲስ አበባ የሚገኘውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽ/ቤት እንደሚጎበኙ፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋራ እንደሚነጋገሩ ታውቋል።

በአፍሪካ ኅብረት በሚኖራቸው ውይይት፣ በአህጉሪቱ የሰዎችን የእንቅስቃሴ ነጻነት ማረጋገጥና ኅብረቱ ተግባራዊ ለማድረግ የወጠነውን የነጻ ንግድ ስምምነት አስመልክቶ እንደሚነጋገሩ ታውቋል። ከዚያም ወደ ጅቡቲ እና ኬንያ ያቀናሉ፤ ተብሏል።

ጀኒቫ ላይ መግለጫ የሰጡት አሚ ፖፕ፣ 80 በመቶ የሚኾነው ፍልሰት ከአፍሪካ እንደሚነሣ አውስተው፣ በተለይ ወደ ባሕረ ሠላጤ ሀገራት የሚሰደዱ ፍልሰተኞች የሚያዙበት መንገድ አሳዛኝ እንደኾነ ገልጸዋል። ለፍልሰተኞች ጥበቃ እንደሚደረግና መሠረታዊ አቅርቦቶችን ስለማግኘታቸው ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው፤ ሲሉ ሓላፊዋ ተናግረዋል።

የሰብአዊ መብቶች ድርጅቱ ሂዩማን ራይትስ ዎች በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት፣ የአገሪቱ የድንበር ጠባቂዎች፣ ከየመን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሊገቡ የሞከሩ በመቶ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ገድለዋል፤ ሲል ክስ አቅርቧል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG