በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“እያንዳንዷን ክፍል እንደ መጨረሻ ክፍል እየሠራን ነው” - “ምን ልታዘዝ”


“እያንዳንዷን ክፍል እንደ መጨረሻ ክፍል እየሠራን ነው” - “ምን ልታዘዝ”
please wait

No media source currently available

0:00 0:11:24 0:00

“እያንዳንዷን ክፍል እንደ መጨረሻ ክፍል እየሠራን ነው” - “ምን ልታዘዝ”

የፖለቲካ ይዘት ባላቸው ጽሑፎች፣ ትችቶች እና ትንታኔዎች ሰዎች ለእስር በሚዳረጉባት ኢትዮጵያ፣ ከአራት ዓመት በፊት “ምን ልታዘዝ” በሚል ርእስ፣ በሀገር ውስጥ ቴሌቭዥን ይተላለፍ የነበረው ምጸታዊ ተውኔት፥ ፖለቲካ ቀመስ መልዕክቶችን፣ አሽሙሮችንና ሽሙጦችን በድራማ መልክ በማቅረብ የብዙ ተመልካቾችን ቀልብ መያዝ ችሎ ነበር።

በወቅቱ የነበረበትን ቅድመ ምርመራ እና ጫና ተቋቁሞ በሦስት ምዕራፍ የተላለፈው “ምን ልታዘዝ” እየበረታ በመጣበት ጫና ቢቋረጥም፣ ከአራት ዓመት በኋላ በአራተኛ ምዕራፍ ወደ ተመልካቹ ተመልሷል።

“ምን ልታዘዝ” የቴሌቭዥን ድራማ፣ ከአምስት ዓመት በፊት በፋና ቴሌቪዥን መተላለፍ ሲጀምር፣ መቼቱ በአንዲት አነስተኛ ካፌ ውስጥ ነበር። አያልቅበት በተሰኘ ገጸ ባሕርይ በሚመራው በዚኽች ካፌ ውስጥ የሚሠሩት ሦስት አስተናጋጆች እና አንድ ባሬስታ፣ እንዲሁም ካፌውን ለመጠቀም የሚገቡ የተለያዩ ሰዎች፣ በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ኹኔታ እንዲያንጸባርቁ ተደርገዋል። በድራማው፥ ከመንግሥት አስተዳደራዊ ችግሮች እና እንከኖች አንሥቶ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ሌሎች በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚብላሉ ችግሮች ይመላለሳሉ፤ ይተቻሉ።

“ምን ልታዘዝ” ከአራት ዓመታት መቋረጥ በኋላ ወደ ተመልካች ሲመለስ፣ ካፌውን ጨምሮ፣ የካፌው ሠራተኞች፣ ተጠቃሚዎች፣ ጋዜጣ አዟሪዎች፣ ሁሉም ማረሚያ ቤት ውስጥ ገብተዋል። ከጀርባው ‘ታራሚ’ የሚል ጽሑፍ የተጻፈበት ተመሳሳይ ልብስም ለብሰዋል። የድራማው ጸሐፊ፣ ዲሬክተር እና ፕሮዲውሰር በኀይሉ ዋሴ፣ የድራማውን መቼት ወደ ማረሚያ ቤት የቀየረው፣ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ሁሉም ሰው ታራሚ በመኾኑ ነው፤ ይላል።

ከሳምንታት በፊት በድጋሚ ወደ ቴሌቪዥን መስኰት የተመለሰው “ምን ልታዘዝ”፣ ከተለመደው ወጣ ባለ መልኩ የመጣበት ፖለቲካዊ ተሣልቆ፣ በተመልካች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን ቢያስገኝለትም፣ ለበርካታ ፈተናዎችም አጋልጦታል። እያንዳንዱ የድራማው ክፍል ከመታየቱ በፊት ይተላለፍበት ከነበረበት የቴሌቭዥን ጣቢያ ከሚያጋጥመው ቅድመ ምርመራ ጀምሮ፣ በርካታ ጫናዎችን እንዳስተናገደም በኀይሉ ይገልጻል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ2010 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን ሲመጡ፣ በፖለቲካ ተሳትፎ፣ በነጻው ብዙኀን መገናኛ እና በሌሎች አፋኝ ሕጎች ላይ የታዩ መሻሻሎች ተመልሰው እንደጠፉ፣ልዩ ልዩ የመብቶች ተሟጋች ተቋማት ይገልጻሉ። በርካታ ጋዜጠኞች፣ ጸሐፊዎች እና ተቺዎችም ለእስር ተዳርገዋል። እነዚኽ ኹኔታዎች ግን፣ በኀይሉን በጽሑፉ ከሚያነሣቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች አልገቱትም። ለዚኽ ደግሞ ምክንያቱ፣ “የአገሬ ጉዳይ ስለሚያገባኝ ነው፤” ይላል።

በ“ምን ልታዘዝ” ድራማ፣ መሪ ገጸ ባሕርይ የኾነውን አያልቅበትን ወክሎ የሚጫወተው ሚካኤል ታምሬ ነው። “ምን ልታዘዝ” በምን መልኩ መመለስ እንዳለበት ብዙ ተወያይተንበታል፤ የሚለው ሚካኤል፣ የማረሚያ ቤት መቼት፣ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ኹኔታ የሚገልጽ ነው፤ ይላል።

ሚካኤል ወክሎ የሚጫወተው አያልቅበት፣ አስተዳዳሪ ወይም በአመራር ላይ ያለ በመኾኑ፣ በርካቶች ገጸ ባሕርይውን፣ አሁን የመንግሥቱን ሥልጣን ይዘው ኢትዮጵያን ከሚመሯት ሹማምንት ጋራ ያመሳስሉታል። የገጸ ባሕርይው ንግግሮች እና ድርጊቶችም፣ ፖለቲካዊ አግቦዎችንና ሽሙጦች ያዘሉ ናቸው። ታዲያ ሚካኤልን፣ “ለእስር ይዳርገኛል ብለኽ አትሰጋም ወይ?” ስል ጠየቅኹት።

ሚካኤልን ግን፣ ከእስር ስጋት ይልቅ የሚሰማው ኩራት ነው። በ“ምን ልታዘዝ” ድራማ ላይ ዋና ገጸ ባሕርይውን ወክሎ በመሳተፉም፣ ራሱን እንደ ዕድለኛ ይቆጥራል።

በኀይሉ ደግሞ፣ “ምን ልታዘዝ”፥ በድራማው ለሚሳተፉ ተዋንያን ብቻ ሳይኾን ለተመልካቹም መተንፈሻ እንዲኾን ይሻል። ዋና ዓላማውም፣ በድራማው ውስጥ የሚነሡ ሐሳቦች እና የሚተላለፉ መልዕክቶች፣ ወደ ተግባር የሚመሩና ለሀገር ህልውና የሚጠቅሙ ሐሳቦችን ማንሸራሸሪያ መድረክ መፍጠር እንደኾነም ይገልጻል።

በዐዲስ መልክ የተመለሰው፣ አራተኛው የ“ምን ልታዘዝ” ምዕራፍ ዘጠነኛ ክፍል ላይ ደርሷል። በሀገር ውስጥ በ“ሀገሬ ቴሌቭዥን” ላይ ከሚከታተለው ተመልካች በተጨማሪ፣ “ምን ልታዘዝ” በሚል የዩቲዩብ ገጹ ላይ፣ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ተመልካቾች በየሳምንቱ በጉጉት ይጠብቁታል። በዚኽ መሀል ታዲያ፣ ዳግም ቢቋረጥስ በሚል የሚሰጉ ጥቂቶች አይደሉም፤ በኀይሉን ጨምሮ።

ከዩኒቨርሲቲ በሰብል ሳይንስ የተመረቀው እና ከፊልም ሥራው ጎን ለጎን ከቤተሰቦቹ ጋራ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን የሚያስተዳድረው በኀይሉ፣ ከ“ምን ልታዘዝ” በተጨማሪ አስኳላ የተሰኘ፣ በዲኤስቲቪ ላይ በ70 ክፍሎች የተላለፈ የቴሌቭዥን ድራማ እና ሌሎችንም የፊልም ሥራዎች ሠርቷል። በሁሉም የኪነ ጥበብ ሥራዎቹም፣ እርሱ ከማኅበረሰቡ የተማረውን፣ የወረሰውንና ያሳደገውን ማጋራት እንደሚፈልግ ይገልጻል።

የፖለቲካ ተሣልቆ ወይም ፖለቲካ ቀመስ ምጸታዊ ተውኔት፣ የፖለቲካ አስተያየቶች እና አመለካከቶች በነጻነት እንዳይንሸራሸሩ በሚከለከልባቸው ማኅበረሰቦች ውስጥ፣ ፖለቲካዊ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ጥቅም ላይ ይውላል። ከ“ምን ልታዘዝ” በተጨማሪ “ግራ እና ቀኝ” የተሰኘ ተመሳሳይ ዘውግ ያለው የቴሌቪዥን ድራማ ላይ እየተጫወተ የሚገኘው ሚካኤል፣ ኢትዮጵያ ላለችበት የፖለቲካ ውጥንቅጥ፣ “የፖለቲካ ተሣልቆ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፤” ይላል።

በወንዶች ማረሚያ ቤት ውስጥ የተመለሰው ምናባዊው “ምን ልታዘዝ” ካፌ፣ በቀጣይ ክፍሎቹ፣ የሴት ታራሚዎችንም እያስተዋወቀ ይቀጥላል። በኀይሉ እንደሚለው፣ እርሱ እና ሁሉም የድራማው ተሳታፊዎች፣ ቢያንስ ሦስት ተከታይ ምዕራፎችን ለመጓዝ ተዘጋጅተዋል። ድራማው መቆየት እስከቻለበት ድረስም ለማኅበረሰቡ የፖለቲካ መተንፈሻ ኾኖ ያገለግላል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG