በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ተመድ የኢትዮጵያ መርማሪ ቡድኑን የሥራ ጊዜ እንዲያራዝም ሂዩማን ራይትስ ዎች ጠየቀ


የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዎች
የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዎች

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት፣ ለኢትዮጵያ ያቋቋመው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መርማሪ ኮሚሽን የሥራ ጊዜ እንዲራዘም፣ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠየቀ።

በኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ከአንድ ዓመት በኋላ፣ አገሪቱ ውስጥ የሚፈጸሙ የጦር ወንጀሎች እና በሰብእና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እንደቀጠሉ፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ ገልጿል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት፣ ለኢትዮጵያ ያቋቋመው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መርማሪ ኮሚሽን፣ ከሳምንት በፊት ያወጣውን ሪፖርት ያስታወሰው ሂዩማን ራይትስ ወች፣ ምክር ቤቱ፣ የኮሚሽኑን የሥራ ጊዜ እንዲያራዝምና ከዚኽ በፊት በተፈጸሙና እየተፈጸሙ ባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ላይ የጀመረውን ዓለም አቀፍ ምርመራ እንዲቀጥል ጠይቋል።

የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቱ፣ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ በተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ተጎጂ የኾኑ ግለሰቦች እና ቤተሰቦቻቸው፥ ትክክለኛ ምርመራ፣ ፍትሕ እና እርማት እንዲደረግ ተደጋጋሚ ጥሪ ማድረጋቸውን ጠቅሶ፣ ይህን ለማስፈጸም ግን፣ በአገራቸው ተቋማት ላይ እምነት እንደሌላቸው አመልክቷል።

ኾኖም፣ የውሳኔ ሐሳቦችን ረቂቅ ለሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ለማቅረብ አንድ ሳምንት ብቻ በቀረበት ወቅት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የመርማሪ ኮሚሽኑ የሥራ ጊዜ እንዲራዘም ይጠይቅ እንደኾን፣ ምንም አመላካች ኹኔታ አለመኖሩን ጠቁሟል።

በመኾኑም፣ “የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መርማሪ ኮሚሽኑ፣ እ.አ.አ በ2021 እንዲቋቋም የተደረጉ ጥረቶችን የመራው የአውሮፓ ኅብረት፣ የሥራ ጊዜው እንዲራዘም ግፊት እንዲያደርግ፣ ተጎጂዎች እና የመብት አቀንቃኞች ይጠይቃሉ፤” ሲል ጥሪ አቅርቧል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች አክሎም፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ በኢትዮጵያ በሚፈጸሙ የመብቶች ጥሰት ላይ የሚደረገው ምርመራ እንዲቀጥል፣ የመርማሪ ኮሚሽኑ ምክረ ሐሳቦች ተግባራዊ እንዲኾኑ በማድረግና በኢትዮጵያ ላይ ለሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ሕዝባዊ ሪፖርት እንዲሰማ የሚጠይቅ የውሳኔ ሐሳብን በማቅረብ፣ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶችን ማስከበርና ተጠያቂነትን ማስፈን አለበት፤ ብሏል።

ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መርማሪ ኮሚሽኑ፣ ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረገው ሪፖርት፣ በትግራይ ክልል የተካሔደው ግጭትም ኾነ የመብቶች ጥሰት እንዳላበቃና ጥቃቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደሚፈጸሙ አስታውቋል። በዐማራ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎችም አካባቢዎች፣ ከፍተኛ ጥሰቶች እየተፈጸሙ እንደኾነና የኢትዮጵያ መንግሥት በነሐሴ ወር የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ከአወጣ በኋላ፣ በዐማራ ተወላጆች ላይ የጅምላ እስር እየተፈጸመ እንደኾነም፣ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አመልክቷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG