ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትግስት አሰፋ በዛሬው ዕለት በበርሊን በተካሄደው የሴቶች ማራቶን የአለም ሪከርድ ሰበሯለች። አትሌት ትግስት ሁለት ሰዓት ከ 11 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ በመግባት ቀድሞ ተይዞ የነበረውን የአለም ሪከርድ በሁለት ደቂቃ አሻሽላለች።
ባለፈው ዓመት ባደረገችው ውድድር የግል ምርጥ አሸናፊ የነበረችው ትግስት አሰፋ ከጎርጎሮሳዊያኑ 2019 አንስቶ በኬኒያዊቷ ብሪጊድ ኮስጌን የሁለት ሰዓት ከ14 ደቂቃ ከአራት ሰከንድ ተይዞ የቆየውን ሪከርድ በማሻሻል በዛሬው ዕለት አዲስ ሪከርድ ሰብራለች።
በውድድሩ አጋማሽ በኋላ በአስደናቂ ፍጥነት መሮጧን ሮይተርስ ዘግቧል። “የአለም ሪከርድ ለመስበር ነበር እየሮጥኩ የነበረው ነገር ግን ይኼንን ሰዓት አስመዘግባለሁ ብዬ አልጠበኩም። ይሄ የከባድ ልፋት ውጤት ነው።” በማለት ከውድድሩ በኋላ ደስታዋን አጋርታለች። ትግስት አሰፋ ቀድሞ የ800 ሜትር ሯጭ ነበረች።
ይህ የዛሬው ውጤት ለፓሪስ ኦሎምፒክ 2024 ኢትዮጵያ እየተዘጋጀች ባለችበት ሰዓት የተደረገ ሲሆን፤ ትግስት አሰፋ በዚህ ውድድር ላይ ትሳተፍ እንደሆነ በጋዜጠኞች ተጠይቃ “አሁን ነጥብ አስመዝግቤያለሁ። ነገር ግን ይሄ ውሳኔ የእኔ ሳይሆን የባለስልጣናቱ ነው። እኔን ለቡድኑ የሚመርጠኝ ብሄራዊ ኮሚቴው ነው።” በማለት ምላሽ ሰጥታለች።
መድረክ / ፎረም