"በባህር ላይ ሲጓዙ ለመስጠም አደጋ የሚጋለጡ ሰዎች መታደግ አለባቸው" ሲሉ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ተናገሩ። አቡነ ፍራንሲስ ይህን ያሉት ፈረንሳይ ውስጥ በምትገኘው ማርሴል ከተማ፣ ለመርከበኞች እና ለስደተኞት በተዘጋጀ መታሰቢያ ላይ ነው።
አቡነ ፍራንሲስ ስደተኞችን ከመታደግ ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት "የጥላቻ ምልክት" ሲሉ ገልፀውታል።
ከአፍሪካ እና ከመካከለኛው ምስራቅ የሚፈልሱ ስደተኞች፣ በሌሎች አካባቢዎች የተሻለ ህይወት ለማግኘት ተስፋ በማድረግ፣ አቅም የሌላቸው ተሰባሪ ጀልባዎችን ተሳፍረው ወደ አውሮፓ ይጓዛሉ። ለአብዛኞቹ የመጀመሪያ መዳረሻቸው በጣሊያን የምትገኘው ላምፔዱሳ ደሴት ብትሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ደሴቷ በሺዎች በሚቆጠሩ ስደተኞች ተጨናንቃለች።
አብዛኛውን ጊዜ ስደተኞቹን የሚያመላልሱት ህገወጥ አዘዋዋሪዎች፣ በጀልባው ላይ ጥለዋቸው የሚሄዱ ሲሆን፣ የነፍስ አድን ተቋማት፣ ስደተኞቹን እንዳይታደጉ በአንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት ይከለከላሉ፣ ወይም የማዳን ተልዕኳቸው ይዘገያል።
"በዚህ ምክንያት ይህ የሚያምር ባህር ትልቅ የመቃብር ስፍራ ሆኗል" ያሉት አቡነ ፍራንሲስ፣ "በርካታ ወንድሞች እና እህቶቻችን በአግባቡ የመቀበር መብት እንኳን ተነፍጓቸዋል" ብለዋል።
የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪው፣ ስደተኞችን የሚታደጉትን ግብረሰናይ ቡድኖችም አመስግነዋል።
መድረክ / ፎረም