በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ላይ የተመሠረተው ክሥ ፖለቲካዊ እና የአገሪቱ የፖለቲካ ሥርዐት የተበላሸ እንደኾነ ያመለክታል፤ ሲሉ፣ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዛሬ ተናግረዋል።
ሩሲያ፣ በትረምፕ ላይ እየኾነ ያለውን “እንደ መልካም ማሳያ ትወሰደዋለች፤” ሲሉ፣ በምሥራቅ ሩሲያ በተዘጋጀ አንድ መድረክ ላይ የተናገሩት ፑቲን፣ ይኸውም፣ የአሜሪካ የፖለቲካ ሥርዐት መበላሸቱን ስለሚያመላክት እንደኾነ አስረድተዋል፡፡ ከዚኽም የተነሣ፣ “አሜሪካ ሌሎችን ስለ ዴሞክራሲ መስበክ አትችልም፤” ሲሉም ፑቲን አክለዋል።
ትረምፕ ለቀረበባቸው ክሥ ሁሉ ጥፋተኛ እንዳልኾኑ ሲያስታውቁ፣ በድጋሚ ለምርጫ እንደሚወዳደሩ የሚጠበቁት ፕሬዚዳንት ባይደን፣ አስተያየት አይሰጡም።
“በአንድ የፖለቲካ ተፎካካሪ ላይ የተፈጸመ በደል ነው። እየኾነ ያለውን፣ አሜሪካውያንም ኾኑ ዓለም በሙሉ እያየ ነው። ውስጣዊ ችግራቸውን አጋልጧል፤” ሲሉ አመልክተዋል ፑቲን።
“ትረምፕ ከሩሲያ ጋራ ልዩ ቁርኝት አላቸው፤” የሚለውን የቆየ ውንጀላም ፑቲን፣ “ሐሰት ነው፤” ሲሉ አጣጥለዋል፡፡
በአሜሪካ ያለው አስተዳደር ሩሲያን፥ “ነባራዊ ጠላት ነች፤” እያለ ለሕዝቡ በመቀስቀሱ፣ በመጪው ምርጫ ማንም ቢያሸንፍ፣ የሩሲያ እና የአሜሪካ ግንኙነት ላይ የሚያስከትለው ጉልሕ ለውጥ እንደማይኖር ፑቲን አስታውቀዋል።
የግል ኩባንያዎች የሚጫወቱትን ሚና አስመልክቶ ፑቲን ሲናገሩ፣ ቢሊየነሩን ኢላን መስክ፥ “ጎበዝ፣ ንቁ እና ተሰጥኦ ያለው ነጋዴ ነው፤” ሲሉ ገልጸውታል።
መድረክ / ፎረም