በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳን ጦር አዛዥ ጀነራል አል ቡርሃን ወደ ኤርትራ አቀኑ


የሱዳን ሠራዊት አዛዥ ጀኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን፣ የኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ
የሱዳን ሠራዊት አዛዥ ጀኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን፣ የኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ

የሱዳን ሠራዊት አዛዥ ጀነራል አብደል ፋታሕ አል ቡርሃን፣ በአገሪቱ በመካሔድ ላይ ባለው ግጭትና በሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ፣ ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈ ወርቂ ጋራ ለመነጋገር፣ ዛሬ ሰኞ ወደ አሥመራ ማቅናታቸውን፣ የአሶሺዬትድ ፕረስ ዜና ወኪል፣ መንግሥታዊ የዜና ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።

መዲናዪቱ ካርቱምንና ሌሎችንም ከተሞች ወደ ጦር አውድማነት በቀየረው ግጭት፣ አል ቡርሃን ዓለም አቀፍ ድጋፍን ሲማፀኑ ቆይተዋል።

በሱዳን መንግሥታዊ የዜና ወኪል “ሱና” ዘገባ መሠረት፣ በጀነራል አል ቡርሃንና በፕሬዚዳንት ኢሳይያስ መካከል፣ ዛሬ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ውይይት፣ በሁለትዮሽ ግንኙነት እና በሱዳን ግጭት ላይ ያተኩራል፤ ተብሏል። ስለ ውይይቱ ተጨማሪ ዝርዝር ጉዳዮች ይፋ አልኾኑም።

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ለዓመታት መልካም እንዳልነበር፣ የአሶሺዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል። ሱዳን፣ ፖለቲካዊ ጥቃትን እየሸሹ ወደ ሀገሯ የገቡ 126ሺሕ ኤርትራውያንን በማስተናገድ ላይ እንደኾነች፣ የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ይገልጻል።

“ቤጃ” የተሰኘውን ጎሣ ጨምሮ፣ በምሥራቃዊ ሱዳን የሚገኙ የጎሣ ቡድኖች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ በፕሬዚዳንት ኢሳይያስ መንግሥት እንደሚደገፍ ይታመናል።

የአል ቡርሃን የአሥመራ ጉብኝት፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ከሀገር ውጭ የተደረገ አራተኛው ዲፕሎማሲያዊ ጉዞ ነው። ባለፈው ሳምንት፣ የኳታሩን አሚር ሼክ ታሚም አል ታኒን ዶሃ ላይ ሲያገኙ፣ ቀደም ብሎ ደግሞ ከግብጹ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታሕ አል ሲሲ፣ እንዲሁም ከደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጋራ ተገናኝተዋል። ጉብኝቶቹን አስመልክቶ የተገኙት መረጃዎች ውስን ናቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሱዳኑ ውጊያ ተፋፍሞ ሲቀጥል፣ ትላንት እሑድ በደረሰ የአየር ጥቃት፣ 43 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በምዕራብ ዳርፉርም፣ ግጭቱ በማንነት ላይ አነጣጥሮ፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና አጋሮቹ የዓረብ ሚሊሺያዎች፣ በጥቁር አፍሪካውያን ላይ ጥቃት እያደረሱ እንደኾነ፣ የሰብአዊ ቡድኖች እና ተመድ ገልጸዋል።

በግጭቱ እስከ አሁን ድረስ ከአራት ሺሕ በላይ ሰዎች እንደተገደሉ ተመድ ሲጠቁም፣ ሐኪሞች እና የመብት አቀንቃኞች በበኩላቸው፣ ቁጥሩ ከተገመተውም በላይ እንደሚኾን በመግለጽ ላይ ናቸው።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG