በሞሮኮ የተለያዩ አካባቢዎች አርብ እለት በደረሰው፣ በሬክተር ስኬል ሲለካ 6.8 የደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ800 በላይ መድረሱን እና 672 ሰዎች ደግሞ መጎዳታቸውን የሞሮኮ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አስታወቀ።
የመሬት መንቀጥቀጡ የደረሰው በሞሮኮ የቱሪስት መዳረሻ ከሆነው ማራካሽ በ72 ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኘው የሞሮኮ አትላስ ተራሮች ላይ ነው።
በማራካሽ የሚገኙ አንዳንድ ህንፃዎች በደርሰባቸው ከፍተኛ መንቀጥቀጥ የወደሙ ሲሆን፣ በርካታ ነዋሪዎች ከቤት ውጪ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው እና፣ ወደተጎዳው መኖሪያ ቤታቸው ለመመለስ ባደረባቸው ፍርሃት ምክንያት ምሽቱን ውጪ ለማሳለፍ መገደዳቸውን ገልፀዋል።
ከነዋሪዎቹ አንዱ የሆነው የ33 አመቱ አብደልሄክ ኤል አምራኒ ስለሁኔታ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ሲገልፅ "ህንፃዎቹ ሲንቀሳቀሱ አያቸው ነበር። ለእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ምን አይነት ምላሽ መስጠት እንዳለብን አናውቅም። ከዛ ወደውጪ ስወጣ፣ ብዙ ሰዎች ቆመው አየሁ" ብሏል።
አብደልሄክ ሰዎች የነበሩበትን ስሜት ሲገልፅም "ሁሉም ሰው በድንጋጤ ውስጥ ነበር" ያለ ሲሆን "ህፃናት ሲያለቅሱ፣ ወላጆች ሲጨነቁ ነበር። ከዛም ሁሉም ሰው ውጪ ለመቆየት ወሰነ" ብሏል።
የመሬት መንቀጥቀጡ እስከ ፖርቹጋል እና አልጄሪያ ድረስ ይሰማ እንደነበር ተገልጿል።
መድረክ / ፎረም