የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለነስኪ ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን በሚገኝ አንድ የገበያ ስፍራ ላይ ባደረግችው ጥቃት በርካታ ሰዎችን መግደሏንና ማቁሰሏን አስታወቁ፡፡
ጥቃቱ የተፈጸመው የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን አስቀድሞ ይፋ ባልተደረገ ጉብኝት ኪቭ በሚገኙበት ወቅት መሆኑን የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል፡፡
“በአሁኑ ጊዜ የሩስያ አሸባሪዎች መድፍ በዶኔትስክ ክልል በምትገኘው ኮስትያንቲኒቪካ ከተማ ውስጥ 16 ሰዎችን ገድሏል፡፡ መደበኛ ገበያ፣ ሱቆችና ፋርማሲ እንዲሁም ምንም ያላደረጉ ሰዎች ብዙ ቆስለዋል "ሲሉ ዘሌንስኪ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ባወጡት ጽሁፍ አስታውቀዋል.
ጠቅላይ ሚኒስትር ዴንስ ሽሚጋል መደዳውን የነበሩ መደብሮች ሲጋዩ እና ሰዎች ከጥቃቱ ሲሸሹ፣ የተሽከርካሪዎች ጡሩምባዎች ድምጽ ሲጮቹ የሚያሳይ የደህንነት ቪዲዮ ምስል መልቀቃቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
የዩክሬን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኢጎር ክላይሜንኮ ጥቃቱ 28 ሰዎችን ቁስለኛ ማድረጉን በማህበራዊ ሚዲያ አስፍረዋል፡፡
ጥቃቱ የደረሰባት ኮስትያንቲኒቪካ በውጊያው ግምባር የምትገኝ ስትሆን ወደ 70ሺ የሚገመት ህዝብ የሚኖርባት የዶኔትስክ ግዛት ምስራቃዊ የኢንደስትሪ ከተማ ናት፡፡
የዶኔትስክ ከፊል ግዛት በዚህ ዓመት ከሩስያ ጋር በኃይል ከተቀላቀሉ ከሶስት ሌሎች አካባቢዎች ጋር እኤአ ከ2014 ጀምሮ በሩሲያ በሚደገፉ ተገንጣዮች ቁጥጥር ስር የሚገኝ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡
መድረክ / ፎረም