በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከሰላም ስምምነቱም በኋላ የኤርትራ ሠራዊት “የጦር ወንጀል ፈጽሟል” ሲል አምነስቲ ከሰሰ


የኤርትራ ካርታ
የኤርትራ ካርታ

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከኢትዮጵያ ጦር ወገን በመሆን ተሳትፎ የነበረው የኤርትራ ጦር፣ ከሰላም ስምምነቱም በኋላ በትግራይ “የጦር ወንጀል እና ምናልባትም በሰብዓዊነት ላይ ያነጣጠረ ወንጀል ፈጽሟል” ሲል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም የሆነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዛሬ አስታውቋል።

ድርጅቱ አክሎ፣ ከሰላም ስምምነቱ በኋላም ሲቪሎች መደፈር፣ ባርነት እና ግድያ እንደሚፈጸምባቸው ገልጿል።

ከሁለት ዓመት በፊት፣ ኤርትራ የኢትዮጵያን ፌደራል ኃይል በመደገፍ ጦሯን ወደ ትግራይ መላኳን ተከትሎ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀብ ተጥሎባት ነበር። ጦሯም በሁለቱ ዓመት ጦርነት በግድያ፣ መድፈር፣ እና ዘረፋ ክስ ሲቀርብበት እንደነበር የኤኤፍፒ ዘገባ አስታውሷል።

በጥቅምት ወር በፌዴራል መንግስት እና በትግራይ አማጽያን መካከል የተፈረመው የሠላም ስምምነት፣ የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ እንዲወጡ የሚጠይቅ ነበር ያለው ሪፖርቱ፣ ኤርትራ የስምምነቱ አካል አለመሆኗን እንዲሁም፣ ጦሯ አሁንም በድንበር አካባቢ እንደሚገኝ ነዋሪዎች በመናገር ላይ መሆናቸውን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታት ለአምነስቲ ቅድመ ሪፖርት መልስ እንዳልሠጡ የሰብዓዊ ድርጅቱ አስታውቆ፣ ሁለቱም መንግስታት ክሱን በተመለከተ ምርመራ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

በአፍሪካ ኅብረት አማካኝነት የተደረሰውን የስላም ስምምነት ያዳክማል በሚል፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ አካላት ምርመራ እንዲደረግ የሚደርገውን ግፊት እንደማትቀበል ስታስታውቅ ቆይታለች፡፡

የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በያዝነው የፈርንጆች ዓመት መጀመሪያ ላይ በናይርቢ፣ ኬንያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ በሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የሚቀርበውን ክስ “ቅዠት” ነው ሲሉ አጣጥለዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG