- ፈረንሣይ ጦሯን በአስቸኳይ እንደምታወጣ ይጠበቃል
በኒዠር አዲስ የተሾሙት ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኤኮዋስ) ጋር ስምምነት ይኖራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ትናንት አስታውቀዋል፡፡ ኤኮዋስ፤ የኒዠር መፈንቅለ መንግስት አድራጊዎች ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ወደ ቦታው የማይመልሱ ከሆነ፣ ቀጠናዊ ሠራዊቱን እንደሚያሰማራ አስጠንቅቆ የነበረ ቢሆንም፣ ወታደራዊው መንግስት ፕሬዝደንቱን እና ሌሎችንም ባለስልጣናት ሾሟል።
“ከኤኮዋስ ጋር ግንኙነት አላቆምንም፣ በመጪው ቀናቶች ውስጥ ስምምነት ላይ እንደርሳለን የሚል ተስፋ አለን” ሲሉ አዲስ የተሾሙት ጠቅላይ ሚኒስትር አሊ ዘይን ትናንት በአንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡
ሁንታው፤ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡትን ፕሬዝደንት ሞሃመድ ባዙምን ባለፈው ሐምሌ ከስልጣን ማስወገዱን ተከትሎ፣ ኤኮዋስ ከበድ ያለ ማዕቀብ ጥሎ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ፈረንሣይ ጦሯን ከኒዠር በአስቸኳይ ታስወጣለች ብለው እንደሚጠብቁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተናግረዋል። በኒዠር መፈንቅለ መንግስት ከተካሄደ ወዲህ፣ በፈረንሣይ ላይ የሚደረገው ተቃውሞ አይሏል። በመዲናዋ ኒያሜይ በሚገኝ የፈረንሣይ ወታደራዊ ሠፈርም ከፍተኛ ተቃውሞ ተካሂዷል።
“ቀድሞውንም የፈረንሣይ ጦር ሀገሪቱ ውስጥ እንዲገባ የፈቀድውን ስምምነት እናወግዛለን። ቆይታቸው ሕገ ወጥ ነው። እያደረግን ያለው ውይይት በአስቸኳይ ከሀገራችን እንዲወጡ ያስችላል” ሲሉ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናግረዋል።
መድረክ / ፎረም