በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኒጀር በመፈንቅለ መንግስቱ ተዘግቶ የቆየውን የአየር ክልሏን ከፈተች


ፋይል - የፈረንሳይ ዜጎች ኒያሚ ከሚገኘው ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በፈረንሳይ ወታደራዊ አውሮፕላን ለመወሰድ ሲጠባበቁ - ነሐሴ 1፣ 2023
ፋይል - የፈረንሳይ ዜጎች ኒያሚ ከሚገኘው ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በፈረንሳይ ወታደራዊ አውሮፕላን ለመወሰድ ሲጠባበቁ - ነሐሴ 1፣ 2023

ኒጀር በሐምሌ ወር የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ ለአንድ ወር እገዳ ተጥሎበት የቆየውን የአየር ክልሏን ዛሬ ሰኞ መክፈቷን የኒጀር ዜና ተቋም የሆነው ኤኤንፒ አስታወቀ።

የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች እ.አ.አ ሐምሌ 26 ስልጣን ከተቆጣጠሩ በኃላ ዘግተውት የነበረውን የአየር ክልል ነሐሴ 2 እንዲከፈት አድርገው የነበረ ቢሆንም፣ የቀጠናው ሀገራት የሲቪል አገዛዝን ለመመለስ ወታደራዊ ጣልቃገብነት እንደሚያካሂዱ ማስፈራራታቸውን ተከትሎ፣ ውሳኔያቸውን በመቀልበስ የአየር ክልሉ ነሐሴ 6 እንደገና እንዲዘጋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

በፕሬዝዳንት ሞሐመድ ባዙም ላይ መፈንቅለ መንግስት ከተደረገባቸው በኃላ፣ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኤኮዋስ) በኒጀር ላይ ማዕቀብ የጣለ ሲሆን፣ ሀገሪቱ ወደ ሲቪል አመራር የማትመለስ ከሆነ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንደመጨረሻ አማራጭ እንደሚጠቀም አስፈራርቷል።

የኒጀር የትራንስፖርት ሚኒስቴር ቃል አቀባይን ጠቅሶ የዘገበው የዜና ተቋም "የኒጀር አየር ክልል ለሁሉም የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ በረራዎች ክፍት ነው" ያለ ሲሆን፣ ሌሎች የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት መቀጠሉንም አመልክቷል።

ዜናው አክሎ፣ የኒጀር አየር ክልል ለማንኛውም ወታደራዊ በረራዎች እና ሌሎች ከሚመለከታቸው ባለስልጣናት ቅድሚያ ፈቃድ ማግኘት የሚገባቸው በረራዎች ግን ዝግ እንደሚሆን ገልጿል።

ከነሔሴ ሁለት ጀምሮ ኒጀር ከጎረቤቶቿ አልጄሪያ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ሊቢያ፣ ማሊ እና ቻድ የሚያገናኟትን የአየር እና የየብስ ድንበሮች ክፍት አድርጋለች። ልዩ ፈቃድ ያገኙ በረራዎችም በዋና ከተማዋ ኒያሜይ የሚገኘውን የአየር ማረፊያ መጠቀማቸውን ቀጥለዋል። ሆኖም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አርብ እለት ባወጣው መግለጫ፣ በድምበር መዘጋት ምክንያት ለኒጀር የሚውል በቶን የሚቆጠር የምግብ እርዳታ መሸጋገሪያ ጣቢያ ላይ መቆየቱን ገልጾ አስጠንቅቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG