በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኪንሻሳው የደን ጉባኤ ለምግብ ዋስትና ደህንነት ጥሪ ተደረገ


ፋይል - ይህ ከሰማይ ላይ የተነሳ ምስል በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ በሚገኘው ሾፖ ግዛት፣ ከኪሳንጋኒ ከተማ 100 ኪሎሜትር ላይ የሚገኘውን 'ያንጋምቢ' ደን ያሳያል
ፋይል - ይህ ከሰማይ ላይ የተነሳ ምስል በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ በሚገኘው ሾፖ ግዛት፣ ከኪሳንጋኒ ከተማ 100 ኪሎሜትር ላይ የሚገኘውን 'ያንጋምቢ' ደን ያሳያል

በማዕከላዊ አፍሪካ የሚገኘውን የዝናብ ደን ለመጠበቅ ያለመ ጉባኤ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ትናንት ማክሰኞ ተጀምሯል፡፡

የጉባኤው ተሳታፊ ተሟጋቾችና የፖለቲካ መሪዎች የደን ጥበቃው ጥረት፣ የአካባቢውን ነዋሪዎች የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ አለበት ሲሉ መከራከራቸውን የፈረንሳይ የዜና ማሰራጫ አውታር የሆነው ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡

1.62 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር (ከ625,000 ስኩዌር ማይል በላይ) የሚሸፍኑት የመካከለኛው አፍሪካ ደኖች ከአማዞን ቀጥሎ ትልቁን የካርቦን ልቀት በመያዝ ሁለተኛ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡

በተጨማሪም ደኖቹ እንደ ዝሆን እና ጎሪላ የመሳሰሉ የደን አራዊትን ጨምሮ የብዝሃ ህይወት መገኛ ሲሆኑ ለከፍተኛ የደን ጭፍጨፋና ውድመት መጋለጣቸው ተገልጿል፡፡

ለሶስት ቀናት በሚቆየው የኪንሳሻው ክልላዊ የመሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ፣ በርካታ ተናጋሪዎች በደኑ ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎች ፍላጎት ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት አሳስበዋል።

“ለተገለሉ እና ለድሃ ህዝቦች ደኑ ገበያቸው ነው” ያሉት የኮንጎ ግብርና ሚኒስትር ጆሴ ምፓንዳ “የሚበሉትን እንዳያገኙ አንከለክላቸውም" ማለታቸው ተዘግቧል፡፡

በአፍሪካ መንግሥታዊ ያልሆነው የምግብ ሉዓላዊነት ድርጅት ዋና አስተባባሪ አቶ ሚሊዮን በላይም እንዲሁ ደኑን ለመጠበቅ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ለተወካዮቹ ተናግረዋል።

"ሰዎች ምግብ ፍለጋ ደኑንን ያወድማሉ" ያሉት አቶ ሚሊዮን "በኮንጎ ተፋሰስ ውስጥ ለደን ጥበቃ ብዙ ድጋፍ አለ፣ ለህዝቡ የምግብ ስርዓት ግን ያለው ድጋፍ በጣም ትንሽ ነው" ማለታቸው ተዘግቧል፡፡

የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ 60 በመቶው የሚሆነው አብዛኛው የኮንጎ ተፋሰስ የዝናብ ደን ያለባት ሀገር ብትሆንም ከዓለማችን ድሃ ሀገሮች አንዷ መሆኗ ተነግሯል፡፡

ኪንሻሳ ባለፈው ዓመት ለነዳጅ እና ለጋዝ አውጭዎች ጨረታ በማውጣቷ ትችት የገጠማት ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አንዳንዶቹ ደኑ ባላበት አካባቢ የሚገኙ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG