በማዕከላዊ አፍሪካዊቷ ሀገር ጋቦን የሚገኙ የጦር መኮንኖች የፕሬዚዳንት አሊ ባንጎን መንግሥት መገልበጣቸውን አስታወቁ።
መኮንኖቹ የመፈንቅለ መንግሥቱን ግልበጣ ዛሬ ማለዳ፣ ያስታወቁት የሀገሪቱ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ፕሬዚዳንት ቦንጎ በሀገሪቱ በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ለሶስተኛ ጊዜ ማሸነፋቸውን ካስታወቁ ከሰዓታት በኋላ፣ በጋቦን የ24 ሰዓት የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት መግለጫ ነው።
የመኮንኖቹ ቃል አቀባይ ባሰሙት መግለጫ "በዛሬው እለት እ.ኤ.አ. ነሐሴ 30 ቀን 2023 እኛ የመከላከያ እና የፀጥታ ኃይሎች፣ በጋቦን ህዝብ እና በጋቦን ተቋማት ጠባቂዎች ስም አሁን ያለውን አገዛዝ በማቆም ሰላምን ለማስጠበቅ ወስንነናል” ብለዋል።
ወታደራዊ ቡድኑ “የምርጫው ውጤት ውድቅ ሆኗል፣ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት ፈርሰዋል፣ ሁሉም ድንበሮች ተጨማሪ መመሪያ እስኪሰጥ ድረስ ዝግ ሆነዋል” ሲል አስታውቋል።
መራጮች ከመኮንኖቹ ማስታወቂያ ቀደም ብለው ሁከት ሊፈጠር እንደሚችል ስጋት አድሮባቸው እንደነበር ተመልክቷል።
ሙሉ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ሊዮቲን የተባሉ የሀገሪቱ ነዋሪ “ያለፈው ጊዜ ያደረጉትን ነገር መልሰው ያደርጋሉ ብለን ፈርተናል። ጠመንጃ! ሀገርን በጠመንጃ መምራት አትችልም። እኛ የጦር መሣሪያዎችን አንፈልግም፡፡” ሲሉ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።
ቦንጎ እኤአ ከ1967 ጀምሮ ፕሬዚዳንት ከነበሩት ከአባታቸው ኦማር ቦንጎ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥልጣን የተረከቡት እኤአ በ2009 እንደነበር ተመልክቷል። መግለጫው በቴሌቭዥን ከተሰማ በኋላ በጋቦን ዋና ከተማ ሊብሬቪል የተኩስ ድምጾች ይሰሙ እንደነበርም ተገልጿል።
በተኩሱ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ግን እስካሁን አልተገለጸም።
መድረክ / ፎረም