ኢትዮጵያዊው ተቃዋሚ ፖለቲከኛ በቀለ ገርባ፣ በኢትዮጵያ መኖር ለህይወታቸው እና ለቤተሰባቸው ደህንነት እንደሚያሰጋቸው በመግለፅ፣ በአሜሪካ የፖለቲካ ጥገኝነት መጠየቃቸውን አስታወቁ።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተቃዋሚ የሆኑት አቶ በቀለ በአፍሪካ ሁለተኛ የህዝብ ብዛት ያላት ሀገር ውስጥ ያለው ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን ገልፀው፣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ዋና ተቃዋምሚ ፓርቲ ሆኖ በሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ (ኦፌኮ) ከነበራቸው የምክትል ፕሬዝዳንትነት ስራ መልቀቃቸውንም ገልፀዋል።
አቶ በቀለ ከፈረንሳዩ የዜና ወኪል አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ጋር አሁን ከሚገኙበት ዩናይትድ ስቴትስ በስልክ ባደረጉት ቆይታ "ወደ ኢትዮጵያ ላለመመለስ ወስኛለሁ። የጥገኝነት ጥያቄዬንም ለአሜሪካ መንግስት አስገብቻለሁ" ብለዋል።
አቶ በቀለ፣ እ.አ.አ በሰኔ 2020 ዓ.ም ከተፈፀመው የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኃላ ተፈጥሮ የነበረውን ሁከት ተከትሎ በቁጥጥር ስር ውለው በሽብርተኝነት እና አመፅ በማነሳሳት ወንጀሎች ተከሰው የነበረ ሲሆን፣ 18 ወራት በእስር ቆይተዋል።
እ.አ.አ በጥር 2022 ዓ.ም ከስር ከተፈቱ በኃላ ባለፈው አመት ሰኔ ላይ ወደ አሜሪካ የመጡ ሲሆን፣ ከዛ በኃላ ወደ ሀገራቸው አልተመለሱም።
"በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ አደገኛ እየሆነ መጥቷል። ማስፈራራት፣ ጅምላ ግድያ እና እስር በሀገሪቱ ሰፍኗል። የፖለቲካ ምህዳሩ በኦፌኮ እንደምንመኘው ሰላማዊ ትግል ለማካሄድ አመቺ አይደለም።" ሲሉ አሁን ያለውን የፖለቲካ ሁኔታም አስረድተዋል።
"ስለዚህ ወደ ኢትዮጵያ የምመለስበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ወሰንኩ" ብለዋል።
አቶ በቀለ እ.አ.አ በ2020 ከመታሰራቸው በፊት፣ ኢትዮጵያን ቀድሞ ያስተዳድር በነበረው እና በትግራይ ክልል ለሁለት አመት የተካሄደው ጦርነት እንዲያበቃ ከአብይ ጋር የሰላም ስምምነት በተፈራረመው፣ የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር የሚመራው ጥምር መንግስትም ሁለት ጊዜ ታስረው ነበር።
"ለህይወቴ እፈራለሁ" የሚሉት አቶ በቀለ "አሁን ያለው ሁኔታ ለህይወት አስጊ ነው። አሁን በቀላሉ እስር ቤት ብቻ የሚያስገቡኝ አይመስለኝም። ደህንነት የለኝም። ቤተሰቦቼም ደህንነታቸው የተጠበቀ አይደልም" ሲሉ ተናግረዋል።
መድረክ / ፎረም