በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የ"አሸንዳ" የሙዚቃ ትርኢት አዘጋጅ በሁከት ማነሣሣት ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀረቡ


በዐዲስ አበባ የተካሄደው፣ የ"አሸንዳ" የሙዚቃ ትርኢት
በዐዲስ አበባ የተካሄደው፣ የ"አሸንዳ" የሙዚቃ ትርኢት

ባለፈው ሳምንት ኀሙስ፣ በዐዲስ አበባ፣ የ"አሸንዳ" የሙዚቃ ትርኢት ያዘጋጁት፣ የ"ፊደል ላውንጅ" ባለቤት አቶ ኤፍሬም ኤርሚያስ፣ በዋና መዲናዋ፣ ሁከት እና ብጥብጥ በማነሣሣት ወንጀል ተጠርጥረው፣ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

አቶ ኤፍሬምን በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ፖሊስ፣ ለምርመራ 14 ተጨማሪ ቀናት እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

የተጠርጣሪው ጠበቆች ደግሞ፣ ደንበኛቸው ቋሚ አድራሻ ያላቸውና የቤተሰብም አስተዳዳሪ በመኾናቸው በዋስ እንዲፈቱ ተከራክረዋል፡፡

ፖሊስ፣ አቶ ኤፍሬምን፥ በርእሰ መዲናዋ ዐዲስ አበባ፣ ሁከት እና ብጥብጥ በማሥነሳት፣ ሀገርንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዐቱን በማወክ ወንጀል እንደጠረጠራቸው ለችሎቱ ገልጿል። ተጠርጣሪው፥ የመንግሥታዊ ሥርዐቱን ገጽታ ለማጠልሸት ሞክረዋ፤ ሲልም፣ ፖሊስ ለፍ/ቤቱ አክሎ አስረድቷል፡፡

የተጠርጣሪው ጠበቆች በበኩላቸው፣ አቶ ኤፍሬም፣ የአሸንዳ የሙዚቃ ትርኢትን ያዘጋጁት፣ በሚሌኒየም አዳራሽ እንደነበረ ጠቅሰው፣ ሓላፊነት የወሰዱትም ለዚኹ ዝግጅት ብቻ እንደኾነና ዝግጅቱም በሰላም እንደተጠናቀቀ ለፍርድ ቤቱ ለፍርድ አስረድተዋል።

በዚያው ዕለት፣ በዐዲስ አበባ ወሎ ሰፈር አካባቢ ተፈጠረ የተባለው ሁከት እና ብጥብጥ፣ የሙዚቃ ትርኢቱ ከተዘጋጀበት አዳራሽ ውጪ በመኾኑ፣ ተጠርጣሪውን እንደማይመለከትና ሓላፊነትም ሊወስዱ እንደማይችሉ ጠበቆቹ ተከራክረዋል፡፡ በሌሎች ሆቴሎች እና የመዝናኛ ስፍራዎችም፣ ተመሳሳይ የአሸንዳ በዓል ዝግጅቶች እንደነበሩ ያወሱት ጠበቆቻቸው፣ አቶ ኤፍሬም፥ በሚሌኒየም አዳራሽ ስለተከናወነው ዝግጅት እንጂ፣ በየመንገዱ ስለኾነው ነገር ሊጠየቁ አይገባም፤ ብለዋል፡፡ በሚሌኒየም አዳራሽ የነበረው ዝግጅት እና በመንገድ ላይ ተፈጠረ የተባለው ሁከትም፣ ግንኙነት እንደሌላቸው አስረድተዋል፡፡

የሚሌኒየም አዳራሹ የአሸንዳ በዓል ዝግጅት፣ በዐዲስ አበባ አስተዳደር ፈቃድ ተሰጥቶት እንደተዘጋጀ የገለጹት ጠበቆቹ፣ ዝግጅቱ በሰላም እንደተጠናቀቀም፣ ለሚመለከታቸው የመንግሥት ቢሮዎች በወቅቱ ሪፖርት እንደተደረገና ተቀባይነትም እንዳገኘ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡

ተጠርጣሪው አቶ ኤፍሬም ኤርሚያስም፣ “በሚሌኒየም አዳራሹ ዝግጅት፣ የተሰበከው ሁሉ ስለ ሰላም ነው። ዝግጅቱ ኀሙስ ዕለት በሰላም ተጠናቆ፣ ዐርብ በቤቴ ነው የዋልኹት። የታሰርኹት ቅዳሜ ዕለት ነው፤" ብለዋል፡፡ "ምንም ዐይነት ችግር ፈጥሬ አላውቅም፤” በማለትም ለፍ/ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ጠበቆቻቸው፣ ተጠርጣሪው አቶ ኤፍሬም፥ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡና ቤታቸውም እንደታሸገባቸው፣ ለችሎቱ ገልጸዋል፡፡

ፖሊስ በበኩሉ፣ ተጠርጣሪውን፣ ትላንት ሰኞ፣ በ48 ሰዓት ውስጥ ወደ ፍ/ቤት እንዳቀረባቸው አስታውቋል፡፡ ቤታቸውን ያሸገውም፣ ምርመራው ባለመጠናቀቁ እንደኾነ አስረድቷል፡፡

የተጠርጣሪውን ቃል ገና እንዳልተቀበለ ያመለከተው ፖሊስ፣ ተጠርጣሪው ከእስር ቢለቀቁ፥ ምርመራውን ሊያሰናክሉ ስለሚችሉ፣ ተፈጠረ በተባለው ሁከት እና ብጥብጥ ምክንያት፣ በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት ካለ ለማጣራት፣ የሰው እና የሰነድ ማስረጃ ለማደራጀት፣ እንዲሁም ወንጀሉ በሀገር ላይ ረብሻ ለመፍጠር የተደረገ በመኾኑ፣ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ፍ/ቤቱን ጠይቋል፡፡

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው፣ አቶ ኤፍሬም የተከሠሡበት ጉዳይ፣ ዋስትና አያስከለክልም፤ በማለት ተከራክረዋል፡፡ ተጠርጣሪው፣ ቋሚ ሥራ እና አድራሻ ስላላቸው፣ የቤተሰብም አስተዳዳሪ ስለኾኑ፣ ትልቅ የሙዚቃ ትርኢት ያዘጋጁና ከዚኽ ቀደም ከነበራቸው ዝንባሌ አኳያ፣ በተፈለጉ ጊዜ መቅረብ ስለሚችሉ፤ እንደዚኹም፣ ተጠርጣሪው በዋስ ቢወጡ፥ ምን ዐይነት መረጃ ሊሰውሩ እንደሚችሉና ፖሊስ ምን ዐይነት መረጃ እንደሚፈልግ በዝርዝር ስላላቀረበ፣ “የደንበኛችን የዋስትና መብት ይከበር” በማለት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም፣ ግራ እና ቀኙን ካዳመጠ በኋላ፣ ለፖሊስ ሰባት ተጨማሪ ቀናትን በመስጠት፣ ለነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

አቶ ኤፍሬም ኤርሚያስ፣ ባለፈው ቅዳሜ፣ በፖሊስ ከተያዙበት ካለፈው ነሐሴ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በዐዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡

የአሜሪካ ድምፅ፣ ከተጠርጣሪው ጠበቆች፣ ከቤተሰቦቻቸው እና ከወዳጆቻቸው፣ ስለ ጉዳዩ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለዛሬ አልተሳካም፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG