የሱዳን ጦር ሠራዊት መሪ ጄኔራል አብደል ፋታህ ቡርሀን፣ እሳቸው በሚመሩት ጦር እና ተቀናቃኛቸው ኮ/ል መሃመድ ሃምዳን ደጋሎ በሚመሩት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል ጦርነት ከጀመረ ወዲህ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ትናንት እሁድ ፖርት ሱዳንን ጎብኝተዋል።
ቡርሃን ካርቱምን በመልቀቅ ፖርት ሱዳን ከመድረሳቸው በፊት የሰሜን አባይ ክፍለ ግዛትን መጎብኘታቸው ተመልክቷል፡፡
ጀኔራሉ ፖርት ሱዳን እንደደረሱ፣ የልዕልና ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ማሊክ አጋር አቀባበል ካደረጉላቸው ባለሥልጣናት መካከል እንደነበሩ ተገልጿል፡፡
ጉብኝቱን አስመልከቶ በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የተሠራጨው የቪዲዮ ምስል ቡርሃን በአገሪቱ ወታደራዊ መኮንኖች አቀባበል የተደረገላቸው መሆኑን አሳይቷል፡፡
በሱዳን ጦር ሠራዊትና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል ካለፈው ሚያዝያ ጀምሮ የተካሄደው ጦርነት ባካርቱም እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች መቀጣጠሉ ተመልክቷል፡፡
በጦርነቱ እስካሁን ከ3.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለመፈናቀል መገደዳቸውን የተባበሩት መንግሥትታ ድርጅት የፍልስተኞ ድርጅት አስታውቋል፡፡ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ ወደ ጎረቤት ሀገራት ግብፅ፣ ቻድ ፣ደቡብ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ እና መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ መሻገራቸውን ድርጅቱ ገልጿል።
ግጭቱ ካርቱምንና ሌሎች የከተማ አካባቢዎችን የጦር አውድማ ሲያደርግ ብዙ ነዋሪዎች ያለ ውሃ እና መብራት ቀርተዋል፡፡ የሀገሪቱ የጤና አጠባበቅ ስርዓትም ሊፈርስ መቃረቡ ተመልክቷል።
መድረክ / ፎረም