በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሩሲያ 42 የዩክሬን ድሮኖችን መትታ መጣሏን አስታወቀች


ዩክሬናውያን በካርኪቭ ዩክሬን የነፃነት ቀንን ሲያከብሩ፣ አንዲት ሴት በጦርነቱ በሞተው ልጇ መቃብር ላይ እያለቀሰች ትታያለች - ነሐሴ 24፣ 2023
ዩክሬናውያን በካርኪቭ ዩክሬን የነፃነት ቀንን ሲያከብሩ፣ አንዲት ሴት በጦርነቱ በሞተው ልጇ መቃብር ላይ እያለቀሰች ትታያለች - ነሐሴ 24፣ 2023

ሩሲያ ከዩክሬን የተላኩ በርካታ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) መደምሰሳቸውን ዛሬ ዓርብ አስታወቀች፡፡

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳመለከተው 42ቱ ድሮኖች የተደመሰሱት ክሬይሚያ ላይ ነው፡፡

ከእነዚህ ዘጠኙ በአየር መከላከያ ተመተው የወደቁ ሲሆን 33ቱ ደግሞ በኤሌክትሮኒክ የጦር መሳሪያዎች መውደማቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

በጥቃቱ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት መኖሩ አልተገለጸም፡፡

በሌላ በኩል የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስቴር (ፔንታገን) ኤፍ 16 የተባሉ ተዋጊ ጀቶችን የሚያበሩ እና የሚጠግኑ ዩክሬናውያንን እንደሚያሰለጥን ትናንት ሐሙስ አስታውቋል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በአሪዞና ክፍለ ግዛት ይሰጣል የተባለው ሥልጠና "የዩክሬንን የረዥም ጊዜ መከላከያን ለማዳበር እና ለማጠናከር የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጥረት ለመደገፍ የሚሰጥ ነው" ሲሉ የፔንታገን ቃል አቀባይ የአየር ኃይሉ ብርጊዴየር ጄኔራል ፓት ራይደር ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኖርዌይ የኤፍ 16 ተዋጊ ጀቶችን ለዩክሬን እየሰጠች መሆኑን ትናንት ሐሙስ ኪቭን የጎበኙት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆናስ ጋህር ስቶሬ ተናግረዋል፡፡

የተዋጊ ጀቶቹ ብዛት ባይገለጽም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምናልባት ከአስር ያልበለጡ ሊሆኑ እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡

ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ለምታካሂደው ውጊያ ተዋጊ ጀቶችን በመለገስ ከኔዘርላንድ እና ዴንማርክ ቀጥሎ ኖርዌይ ሶስተኛዋ የአውሮፓ አገር መሆኗ ተነግሯል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG