በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሊቢያ መረጋጋት ከፍተኛ አደጋ ላይ ወድቋል


የሊቢያ የጸጥታ ኃይሎች በትሪፖሊ በተጠንቀቅ ቆመው - ነሐሴ 10፣ 2015
የሊቢያ የጸጥታ ኃይሎች በትሪፖሊ በተጠንቀቅ ቆመው - ነሐሴ 10፣ 2015

በሊቢያ በሚሊሻዎች መካከል በቅርቡ የደረሰው ግጭት፣ እንዲሁም በጎረቤት ሀገራት ሱዳን እና ኒጀር እየተካሄደ ያለውና በቀላሉ በነዳጅ ዘይት ወደበለፀገችው ሀገር ሊዛመት በሚችለው ግጭት ምክንያት፣ የሀገሪቱ መረጋጋት ከፍተኛ አደጋ ላይ መውደቁን በሊቢያ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ማክሰኞ እለት አስታወቁ።

ልዩ መልዕክተኛው አብዱላይ ባቲሊ ለመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክርቤት እንደተናገሩት በሊቢያ የሚታየው የፖለቲካ መከፋፈል "ከፍተኛ ሁከት እና የሀገሮች መበታተን አደጋ ጋርጧል።" በሀገሪቱ የሚገኙ ተቀናቃኝ ቡድኖችም ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን እንዲፈቱ እና ለረጅም ጊዜ የዘገየው ድምፅ የመስጠት ሂደት እንዲካሄድ አሳስበዋል።

"በቀጠናው ያለውን መረጋጋት ለመጠበቅ፣ በሊቢያ መረጋጋት መስፈኑ መሰረታዊ ነው" ያሉት ልዩ መልዕክተኛው፣ "በሊቢያ ውስጥ ሰላማዊ፣ ሁሉን አቀፍ እና ግልጽነት ያለው ምርጫ እንዲካሄድ መንገድ የሚከፍት ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ስምምነት ከሌለ ሁኔታው ተባብሶ በሊቢያ ሕዝብ ላይ ተጨማሪ ስቃይ ያስከትላል" ብለዋል።

እ.አ.አ በ2011 ዓ.ም በሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት(ኔቶ) በተደገፈ ሕዝባዊ አመፅ፣ ለረጅም ጊዜ አምባገነን መሪ ሆነው የቆዩት ሞአመር ጋዳፊ ከተገደሉ ወዲህ፣ ሊቢያ ከፍተኛ ትርምስ ውስጥ ቆይታለች።

በቅርቡ የተነሳው የፖለቲካ ቀውስ የመነጨው ግን እ.አ.አ በታህሳስ 24፣ 2021ዓ.ም እንዲካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ምርጫ ከከሸፈና በዋና ከተማዋ ትሪፖሊ የተካሄደውን የሽግግር መንግስት የመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱል ሀሚድ ዴቢባህ ከስልጣን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተከትሎ ነው። በምላሹ፣ መቀመጫውን በምስራቅ ሊቢያ ያደረገው ፓርላማ ተቀናቃኛቸውን ፋቲ ባሻጋ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሾሞ የነበረ ሲሆን፣ ከግንቦት ወር ወዲህ ግን ከስልጣን ታግደዋል።

ባታሊ በፀጥታው ምክርቤት ባደረጉት ንግግር በሊቢያ በቋፍ የነበረው መረጋጋት ከነሐሴ 8-9 በተቀናቃኞቹ ሚሊሻዎች መካከል በተካሄደው እና የ55 ሰዎችን ህይወት ባጠፋው ግጭት ተናግቷል። ንፁሃን ዜጎችን ጨምሮ ከመቶ በላይ ሰዎችም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ሚሊሻዎቹ በትሪፖሊ ያደረጉትን ግጭት አውግዘው፣ በሱዳን እና በኒጀር ያለው አለመረጋጋት ሰፊ ወደሆነ ሁከት ሊዛመት እንደሚችል ገልፀዋል።

ባታሊ በበኩላቸው ሊቢያ ከሱዳን ጋር የምትጋራው ድንበር፣ ለታጣቂዎች፣ ቅጥረኛ ተዋጊዎች፣ በህግወጥ ስደት ለተሰማሩ የተደራጁ ወንጀለኞች፣ ህገወጥ ማዕድን አውጪዎች፣ አደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪዎች እና ሌሎች የወንጀል ድርጊቶች ክፍት ሆኖ መቆየቱን አመልክተዋል።

ሌላዋ ጎረቤት ሀገር ኒጀርም እንዲሁ በሊቢያ አለመረጋጋት መጎዳቷን እና የተወሰኑ ኒጀራውያን በሊቢያ የሚገኙ ቅጥረኛ ትዋጊዎችን እና ታጣቂዎችን መቀላቀላቀላቸውን የገለፁት ባታሊ፣ የኒጀር ጦር ከተበታተነ በኒጀር የሚፈጠረው አለመረጋጋት በሊቢያ ላይም ተመሳሳይ መዘዝ እንደሚያስከትል አስጠንቅቀዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG