የዩናይትድ ስቴትስ፣ የጃፓን እና የደቡብ ኮሪያ መሪዎች አርብ ዕለት በፕሬዘዳንታዊ የመዝናኛ ስፍራ ካምፕ ዴቪድ የነበራቸውን የመሪዎች ስብሰባ፤ የሦስትዮሽ የትብብር ቃልኪዳን በመግባት አጠናቀዋል። የሦስቱ ሀገራት መሪዎች በቻይና እና በሰሜን ኮርያ ተደቅኗል ያሉትን ቀጠናዊ ቀውስ በተመለከተ በጋራ ለመስራትም ተስማምተዋል።
“ከማናቸውም ምንጮች የሚጋረጡ አደጋዎችን በተመለከተ በፍጥነት እርስ በርስ ለመማከር ቆርጠናል” ሲሉ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ከደቡብ ኮሮያው አቻቸውን ፕሬዘዳንት ዮንሱክ ዮኤል እና የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፋሚዮ ኪሺዳ ጋር በጥምረት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
ባይደን “ይሄ ማለት ሀገሮቻችንን የሚጎዳ ቀጠናዊ ቀውስ በማናቸውም ጊዜያት ሲከሰት ምላሻችንን የሚያስተባብር እና መረጃዎችን የሚያሰባስብ የነጻ የስልክ መስመር ይኖረናል ማለት ነው።” ሲሉ አክለዋል።
መሪዎቹ ባለፉት ጊዜያት ካደረጓቸው ስብሰባዎች ለየት ባለ መልኩም ባወጡት የጋራ መግለጫ ላይ “አደገኛ፣ በጉልበት እና ህገወጥ በሆነ መልኩ የባህር ላይ ይገባኛል ባይነት” በማለት የቤጂንግን በደቡባዊ ቻይና የባህር አካል ላይ ያላትን እንቅስቃሴ አስፍሯል።
ቻይና በቀጠናው የባህር አካል ላይ ብሩናይ፣ ማሌዢያ፣ ፊሊፕንስ ታይዋን እና ቪየናምን በመቃረን ሁሉም የውሃ አካል ሉዓላዊ ግዛቴ ነው ትላለች። ይሁን እንጂ በጎርጎሮሳዊያኑ 2016 የተካሄደው አለም አቀፍ ችሎት ይህ የቻይና ተግባር የሕግ መሰረት የሌለው ነው ሲል በይኗል።
መድረክ / ፎረም