በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የትረምፕን ክሥ አስመልክቶ ዝንቅ አስተያየቶች እየተሰጡ ናቸው


የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ፣
የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ፣

የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ፣ “የ2020ን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት ለመቀልበስ ሞክረዋል” በሚል ለአራተኛ ጊዜ መከሠሣቸውን አስመልክቶ፣ በመላ አሜሪካ፣ ዝንቅ አስተያየቶች በመሰጠት ላይ ናቸው።

በጆርጂያ ክፍለ ግዛት፣ ከሕዝብ የተውጣጡ ዳኞች(Grand Jury)፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት፣ በ41 ዝርዝር ጉዳዮች በሕግ ሊጠየቁ እንደሚችሉ፣ ከትላንት በስቲያ ሰኞ አስታውቀዋል።

ከአሜሪካ ዋና መዲና ዋሽንግተን ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው አርሊንግተን፣ ቨርጂኒያ የሚገኙ እና የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች፣ ትረምፕ የገጠማቸውን የሕግ ተጠያቂነት ፈተና አስመልክቶ ያላቸው አስተያየት፣ የቀላቀለ ነው።

“ለሀገሪቱ ጥሩ አይደሉም፤ የሚሰጣቸውም ቅጣት መልሰው ለፕሬዚዳንትነት እንዳይወዳደሩ የሚያስቆማቸው ይኾናል ብዬ ተስፋ አደርጋለኹ፤” ስትል፣ መሊሳ ፍሬይ የተባለች ነዋሪ አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡

“የቀድሞ ፕሬዚዳንት፣ በማልኖርበት ከተማ ውስጥ ችግር ውስጥ ከመግባታቸው አብልጦ የሚያንገበግቡኝ ብዙ ጉዳዮች በሕይወቴ አሉ። ስለዚኽ፣ ለወሬው እምብዛም ትኩረት አልሰጠኹትም። ስለ እርሳቸው፣ ምንም ግድ የለኝም፤” ያለው ደግሞ ጀሲ ኽርናንደዝ ነው።

“የትረምፕ ደጋፊዎች፣ ክሡን ከምር የሚወስዱት አይመስለኝም። በፕሬዚዳንቱ የምርጫ ዘመቻም ላይ ተጽእኖ የሚኖረው አይመስለኝም። ምክንያቱም፣ ደጋፊዎቹ ኹል ጊዜም ይደግፋሉ፤ ለዚያውም እጅግ በከረረ መንገድ!” ያለችው ደግሞ ዬሊን ሮደሪከዝ ነች።

“የክልል ዐቃብያነ ሕግ፣ ጥፋት ፈጽሞ የተገኘን ሰው፣ ማድረግ የሚገባቸው ነገር አለ። የቀድሞው ፕሬዚዳንት፣ የተከሠሡበትንም ኾነ ጥፋተኛ በተባሉበት ጉዳይ፣ ምንም ሳይደረጉ ቆይተዋል፤” ያሉት ሌላው ነዋሪ ደግሞ ዳሪን ማርሻል ናቸው።

የዴሞክራቲክ ፓርቲው መሪዎች፣ የትረምፕን ለሕግ ተጠያቂነት መቅረብ፣ ማንም ሰው ከሕግ በላይ እንዳልኾነ አመላካች ነው፤ ይላሉ። አንዳንድ የሪፐብሊካን ፓርቲው መሪዎች በበኩላቸው፣ ክሡ፥ ፖለቲካዊ እና የ2024ቱ ምርጫ መሪ ተፎካካሪ በኾኑት ላይ ያነጣጠረ እንደኾነ ይናገራሉ፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG