በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሊቢያ 55 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ተኩስ አቁም ስምምነት ተደርጓል


በትሪፖሊ ተፋላሚ ወገኖች መካከል በተፈጠረው ግጭት የደረሰ ቃጠሎ እአአ ነሃሴ 15/2023
በትሪፖሊ ተፋላሚ ወገኖች መካከል በተፈጠረው ግጭት የደረሰ ቃጠሎ እአአ ነሃሴ 15/2023

በሊቢያ 55 ስዎች ከሞቱና ሌሎች 146 ከቆሰሉ በኋላ ተኩስ ማቆሙ የጸና ይመስላል ሲሉ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ መሆናቸውን የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።

በሊቢያ ተፋላሚ ወገኖች፣ ማለትም በ444ኛ ብርጌድ እና በአል-ራዳ ኃይሎች መካከል ከሰኞ እስከ ትናንት ማክሰኞ ድረስ ትሪፖሊ ውስጥ ከፍተኛ ውጊያ ተደርጎ ነበር።

ከ12 ዓመታት በፊት ሀገሪቱን ለረጅም ዓመታት የገዙት ሞአመር ጋዳፊ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ፣ ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ያዝ ለቀቅ እያደረጉ ሥልጣኑን ለመያዝ ሲዋጉ ከርመዋል።

በቅርቡ አንጻራዊ መረጋጋት ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን፣ ይህም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዚህ ዓመት ምርጫ ይደረጋል የሚል ተስፋ እንዲኖረው አድርጎ ነበር።

ግጭቱ የተለኮሰው የ444ኛ ብርጌድ መሪ ኮሎኔል ማህሙድ ሃምዛ በተቀናቃኙ አል-ራዳ ኃይሎች መያዛቸውን ተከትሎ መሆኑን የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር አስታውቋል። ኮለኔሉ ለገለልተኛ ወገን እንዲተላለፉ በተመድ እውቅና ከተሰጠውና፣ በትሪፖሊ ከሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስትር አብደልሃሚድ ደቢባ መንግስት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን የአል-ራዳ ኃይሎች አስታውቀዋል።

ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ከጠቅላይ ሚኒስትር ደቢባ መንግስት ጋር ስምምነት እንዳላችው ተመልክቷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG