በዐማራ ክልል፣ እስከ ስድስት ወር ተፈጻሚ እንዲኾን በሚኒስትሮች ም/ቤት የታወጀውና ዛሬ ሰኞ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ፣ “ካለፉት አምስት ዓመታት ስሕተቶቻችን ያለመማራችን ውጤት ነው፤” ሲሉ፣ የቀድሞው የዐማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ተቃውሟቸውን ገለጹ፡፡
በአሁኑ ወቅት፣ በዐማራ ክልል የተስፋፋው ችግር መሠረታዊ ምክንያት፣ የብልጽግና መንግሥት የፖለቲካ አመራር ክፍተት ነው፤ ያሉት አንዱ የፓርቲው መሥራች አቶ ገዱ፣ ራሱ የሚፈጥራቸውን ፖለቲካዊ ችግሮች፣ በወታደራዊ ኀይል መፍታት የመንግሥት ባሕርይ ኾኗል፤ ሲሉ ተችተዋል፡፡
አቶ ገዱ ይህን ተቃውሟቸውን ያሰሙት፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ረቂቅ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ በቀረበበት ወቅት ነው፡፡
የምክር ቤቱ አባላት፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን በመደገፍ እና በመቃወም ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል፤ ስድስት የምክር ቤቱ አባላት ያሉበት፣ “የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መርማሪ ቦርድ”ም ሠይሟል፡፡ በምሽቱ ሦስት ሰዓት የዜና እወጃ ዝርዝር ይቀርባል።
መድረክ / ፎረም