በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

መንግሥታዊ ያልኾነው ድርጅት 76 ፍልሰተኞችን ከባሕር ላይ አደጋ ታደገ


“የፍልሰተኞች ሞት እየጨመረ መኾኑ ለሰው ልጅ ከባድ ቁስል ነው” - /አባ ፍራንሲስ/

አንድ መንግሥታዊ ያልኾነ ድርጅት፣ ባለፈው ዐርብ፣ 76 የሚደርሱ ፍልሰተኞችን ከማልታ የባሕር ዳርቻ እንደታደገ ሲያስታውቅ፣ 24ቱ ሕፃናት እንደነበሩና ከእነርሱም 12ቱ ያለዐዋቂ አጃቢ ብቻቸውን እንዳገኛቸው ገልጿል፡፡

ሕፃናቱም ከግብጽ፣ ከኤርትራ፣ ከኢትዮጵያ እና ከሶርያ እንደመጡ ታውቋል። ፍልሰተኞቹ፣ ከዕንጨት በተሠራ ጀልባ ላይ ኾነው ከሊቢያ እንደተነሡና ቆይተውም የድረሱልን ጥሪ እንዳሰሙ ተገልጿል።

ከአደጋ የተረፉት ፍለሰተኞች፣ የሕክምና ርዳታ እንደተደረገላቸውና ዛሬ ጠዋት ኔፕልስ ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ የአሶሺዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።

በተመሳሳይ ዜና፣ በርካታ ፍልሰተኞች፣ በደርዘን በሚቆጠሩ ጀልባዎች እየኾኑ፣ ባለፉት ሁለት ቀናት፣ ወደ ሦስት አነስተኛ የጣሊያን ደሴቶች እንደደረሱ ታውቋል። እኒኽም፣ በሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች አማካይነት፣ ከቱኒዚያ የተነሡ እንደኾነ ተነግሯል።

ባለፉት 10 ቀናት፣ በርካታ የጀልባ አደጋዎች፣ በሜዲትሬንያን ባሕር ላይ መድረሳቸውን፣ ሪፖርቶች አመልክተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሮማ ካቶሊክ ፖፕ አባ ፍራንሲስ፣ ትላንት እሑድ በነበረ የጸሎት ሥነ ሥርዐት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ፍልሰተኞቹ ላለፉት ተከታታይ ቀናት ለሞት እየተዳረጉ መኾኑ፣ “ለሰው ልጅ ከባድ ቁስል ነው፤” ብለዋል።

ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ ብቻ፣ ሁለት ሺሕ የሚደርሱ ፍልሰተኞች፣ በሜዲትሬንያን ባሕር ላይ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG