በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር፣ መንግሥታቸው፥ “ኤርትራ፣ ጦሯን፣ ከትግራይ ሙሉ ለሙሉ አውጥታ ወደ ድንበሯ ትመልስ፤” የሚለውን ጥሪ እንደሚደግፍ መግለጻቸውን ተከትሎ፣ ኤርትራ፥ በአገሯ የሚገኙትን የእንግሊዝ አምባሳደር ጠርታ ማነጋገሯ ታውቋል።
የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ አብ፣ በቀድሞው የትዊተር በአሁኑ “X” ማኅበራዊ ትስስር መድረክ ላይ ባወጡት ጽሑፍ፣ የአገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የእንግሊዙን ጉዳይ አስፈጻሚ፣ ትላንት ኀሙስ ስለጠራበት ምክንያት አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ዴረን ዌልች፣ “የህወሓትን ያልተገባ ፍላጎት የሚደግፍ መሠረተ ቢስ አስተያየት ተናግረዋል፤” ያሉት የማስታወቂያ ሚኒስትሩ፣ በኤርትራ የእንግሊዙ ጉዳይ ፈጻሚ የተጠሩት፣ “ጠንካራ የተቃውሞ መልዕክት ለማስተላለፍ ነው፤” ብለዋል።
በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደሩ፣ ከህወሓት ጋራ ግንኙነት ላለው ትግራይ ቴቪ በሰጡትና ከትላንት በስቲያ ረቡዕ በኢንተርኔት በወጣው ቃለ ምልልሳቸው፣ “የኤርትራ ኀይሎች፣ ሙሉ በሙሉ ወደ ራሳቸው ድንበር እንዲመለሱ የሚደረገውን ጥሪ፣ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ይደግፋል፤” ብለዋል።
ለሁለት ዓመታት በዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ መንግሥት ኀይሎች ጎን ኾነው የተዋጉ ሲኾን፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና የመብት ቡድኖች፣ በጦርነቱ ወቅት፣ የጭካኔ አድራጎትን በመፈጸም ወንጅለዋቸዋል።
ጦርነቱ፣ ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ፣ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ ላይ በተደረሰውና ከኢትዮጵያ ጦር በቀር የባዕዳን ኀይሎች በሙሉ፣ ከትግራይ ክልል እንዲወጡ በሚጠይቀው ስምምነት ተቋጭቷል፡፡ ይኹንና፣ በስምምነቱ ያልተሳፈተችው የኤርትራ ወታደሮች፣ አኹንም፣ በትግራይ የድንበር አካባቢዎች መኖራቸውን፣ የአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ አክሎ አመልክቷል።
መድረክ / ፎረም