በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የምግብ ርዳታ እንዳልቀጠለ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አስታወቀ


WFP
WFP

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ለሦስት ወራት አቋርጦት የነበረውን የምግብ ርዳታ መቀጠሉን ቢናገርም የክልሉ የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚሽነር የምግብ ርዳታው አሁንም የተቋረጠ መኾኑን ተናገሩ፡፡

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚሽነር፣ ዶክተር ገብረ ህይወት ገብረ እግዚአብሄር ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃል የምግብ ርዳታው ከታገደበት መጋቢት ወዲህ ከሰባት ዞኖች በሦስቱ ከረሃብ ጋር በተያያዘ የ1411 ሰዎች ህይወት ማለፉን መዝግበናል ብለዋል፡፡

የዓለም የምግብ ፕሮግራም በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የምግብ ርዳታ መቀጠሉን ያስታወቀው ባለፈው ማክሰኞ ነበር፡፡ በርዳታ ወደ ሀገር ውስጥ የገባ እህል “ተሰርቋል” በሚል፣ ከአራት ወራት በፊት፣ በኢትዮጵያ፣ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የሚሰጠውን የምግብ ርዳታ አቋርጦ የነበረው የዓለም የምግብ ፕሮግራም በአንዳንድ ቦታዎች፣ በአነስተኛ መጠን ርዳታ በማከፋፈል ላይ እንደኾነ ገልጾ በማሠራጨቱ ሒደት ውስጥ፣ መንግሥት፣ አሁንም ሚና እንዳለው አስታውቋል።

የአሜሪካ መንግሥት በበኩሉ፣ በአካባቢ ባለሥልጣናት ቁጥጥር ሥር የነበረውን የርዳታ እደላ አስመልክቶ፣ ከመንግሥት ጋራ እየተደራደረ በመኾኑ፣ የምግብ ርዳታ የማቋረጡ ውሳኔ አሁንም በተግባር ላይ እንዳለ አስታውቋል።

የምግብ ርዳታ መቋረጡ፣ 20 ሚሊዮን የሚኾኑ ወይም ከአጠቃላይ ሕዝቡ አንድ ስድስተኛውን ሕዝብ፣ እንዲሁም 800 ሺሕ ስደተኞችን ችግር ላይ ጥሏል፤ ተብሏል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG