- በግጭቱ በርካታ ሰዎች ለሞት እና ጉዳት ተዳርገዋል
በዐማራ ክልል፣ በመከላከያ ኀይሎች እና በአካባቢው የፋኖ ታጣቂ መካከል፣ ለቀናት ከተካሔደ የትጥቅ ግጭት በኋላ፣ የፌዴራል መንግሥት፣ ታጣቂዎቹን ከከተሞች እንዳስወጣ ማስታወቁን ተከትሎ፣ አብዛኛው የዐማራ ክልል ክፍል፣ ዛሬ ኀሙስ፣ ወደ መረጋጋት እንደተመለሰ፣ የክልሉ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በክልሉ በነበረው ሁከት፣ ምን ያኽል ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ እስከ አሁን ይፋ የተደረገ አኀዛዊ መረጃ ባይኖርም፣ በሆስፒታል የሚያገለግሉ የሕክምና ባለሞያዎች፣ በርካታ ንጹሐን ዜጎች እንደተገደሉና ጉዳት እንደደረሰባቸው ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የሚሠሩ አንድ ሐኪም፣ ለዜና ወኪሉ በሰጡት መረጃ፣ ወደ ሕክምና ተቋሙ ከገቡ ሰዎች መካከል፣ 20 ሰዎች እንደሞቱ፣ በአብዛኛው ንጹሐን ዜጎች የኾኑ 190 ሰዎች ደግሞ፣ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።
ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት እኚኽ ሐኪም፣ በሆስፒታሉ፣ ምግብ እና መድኃኒት እያለቀ እንደኾነ አመልክተዋል፡፡ በኦክሲጅንና በደም እጥረት ምክንያት፣ በሆስፒታሉ የሚገኙ ታካሚዎች ሕይወት እያለፈ እንዳለም ገልጸዋል።
በተመሳሳይ፣ በባሕር ዳር ፈለገ ሕይወት ሆስፒታል የሚሠሩ ሌላ ሐኪም፣ ጉዳት የደረሰባቸው 130 ሰላማዊ ዜጎች፣ ወደ ሆስፒታሉ እንደገቡ ጠቅሰው፣ ከእኒኽም ውስጥ የ10 ጉዳተኞች ሕይወት እንዳለፈ ተናግረዋል። “ሰዎች በመንገድ ላይ ሊደርስባቸው የሚችለውን አደጋ ተጋፍጠው፣ የተጎዱ ቤተሰቦቻቸውን ተሸክመው፣ በእግር ወደ ሆስፒታሉ ይመጣሉ፤” ያሉት ሐኪሙ፣ በከተማው ውስጥ ከፍተኛ ስጋት ከመስፈኑ የተነሣ፣ አምቡላንሶች ሥራ ማቆማቸውን አመልክተዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም በጎ አድራጎት ተቋም የኾነው የሕፃናት አድን ድርጅት(SAVE THE CHILDREN)፣ ትላንት ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፣ በዐማራ ክልል የሕፃናት ሕይወት በቋፍ ላይ እንደኾነ አመልክቶ፣ ተፋላሚ ወገኖች፣ ሰብአዊ ርዳታ ይደርስ ዘንድ እንዲፈቅዱ ጠይቋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት፣ በክልሉ የጣለውን እስከ ስድስት ወር ሊቆይ የሚችል የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ አፈጻጸም የሚቆጣጠረው የጠቅላይ መምሪያ ዕዝ፣ በስድስት ከተሞች - ባሕር ዳር፣ ላሊበላ፣ ጎንደር፣ ሸዋሮቢት፣ ደብረ ብርሃንና ደብረ ማርቆስ - ለሁለት ሳምንት የሚቆይ ሰዓት እላፊ ዐውጇል፡፡ በዐዲስ አበባ፣ 14 ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር እንዳዋለም፣ በትላንት መግለጫው አስታውቋል።
በሰዓት እላፊው መሠረት፣ ከአስቸኳይ ጊዜ እና የጸጥታ ኀይሎች ተሽከርካሪዎች በቀር፣ ሌሎች ተሽከርካሪዎች፣ ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ እንዳይንቀሳቀሱ ሲታገዱ፣ ሕዝባዊ ስብሰባዎች እና ሰልፎችም ተከልክለዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ፣ በክልሉ ዋና መዲና ስለታሰሩት ሰዎች፣ እስከ አሁን የሰጠው መረጃ ባይኖርም፣ በቃሉ አላምረው የተባለ የማኅበራዊ ብዙኀን መገናኛ ጋዜጠኛ፣ ከመኖሪያ ቤቱ ተወስዶ በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ እንደታሰረ፣ ቤተሰቦቹ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።
“አልፋ ቲቪ” የተሰኘው የዩቲዩብ ቻናል መሥራች እና ዋና አዘጋጅ በቃሉ፣ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወዲህ ሲታሰር፣ የአኹኑ ለአራተኛ ጊዜው እንደኾነ፣ የቤተሰቡ አባል አክለው ገልጸዋል። የበቃሉ እስር፣ በዐማራ ክልል እየተካሄደ ካለው ግጭት ጋር ይያያዝ እንደኾን፣ እስከ አሁን አልታወቀም።
ነዋሪነቱ በባሕር ዳር የኾነ ተስፋሁን የተባለ ግለሰብ፣ አሁን ከተማዪቱ ስላለችበት ኹኔታ ሲገልጽ፣ “ዛሬ ከተማዋ ጸጥ ረጭ ብላለች፡፡ ማንም የሚንቀሳቀስ የለም፤” ብሏል፡፡ “የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ በከተማዋ ውስጥ እየተዘዋወረና ተጠርጣሪዎችን ለመፈለግ በሚል ወታደሮች፣ ቤት ለቤት እየዞሩ ፍተሻ እያካሔዱ ነው፤” ብሏል።
በአሁኑ ሰዓት፣ ምንም ዐይነት የተኩስ ድምፅ እንደማይሰማ የገለጸው ተስፋሁን፣ በግጭቱ ምክንያት የተገደሉ ንፁሐን ዜጎች የቀብር ሥነ ሥርዐት፣ በባሕር ዳር ከተማ አብያተ ክርስቲያናት እንደተፈጸመ ተናግሯል።
በላሊበላ እና በክልሉ ሁለተኛ ትልቁ ከተማ ጎንደር የሚገኙ ነዋሪዎችም፣ ተመሳሳይ ኹኔታ መኖሩን ሲገልጹ፣ ፋኖ በመባል የሚጠሩት ታጣቂዎች፣ ከከተሞቹ እየወጡ እንዳፈገፈጉ፣ ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።
/በዐማራ ክልል ያለው ወቅታዊ ኹኔታ በተመለከተ ዘጋቢያችን መስፍን አራጌ ስለ አካባቢው በስልክ የሰጠን መረጃ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ/
መድረክ / ፎረም