በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትግራይ ክልል ስምንት ወረዳዎች የአንበጣ መንጋ እንደተከሠተና ጉዳትም ማድረስ እንደጀመረ ተገለጸ


በትግራይ ክልል ስምንት ወረዳዎች የአንበጣ መንጋ እንደተከሠተና ጉዳትም ማድረስ እንደጀመረ ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:02 0:00

በትግራይ ክልል ስምንት ወረዳዎች የአንበጣ መንጋ እንደተከሠተና ጉዳትም ማድረስ እንደጀመረ ተገለጸ

በትግራይ ክልል ስምንት ወረዳዎች፣ የአንበጣ መንጋ መከሠቱን፣ የክልሉ ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ገለጸ፡፡አስተያየታቸውን ለአሜሪካ ድምፅ የሰጡ አርሶ አደሮች፣ የአንበጣ መንጋው፣ በአዝርዕት ላይ ሊያደርስ ከሚችለው አንጻር፣ በቀጣይ ከፍተኛ ስጋት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

በትግራይ ክልል፣ ከሐምሌ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ፣ የአንበጣ መንጋ እንደተከሠተ፣ የክልሉ የግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ገልጿል፡፡ በቢሮው የዕፀዋት ጤና ክሊኒክ እና ተባይ መከላከል ቡድን መሪ አቶ ገብረ ሕይወት ኀይለ ሥላሴ፣ ለአሜሪካ ድምፅ እንደገለጹት፣ የአንበጣ መንጋው እስከ አሁን፣ በኹለት ዞኖች ሥር በሚገኙ ስምንት የክልሉ ወረዳዎች መታየቱን ገልጸዋል፡፡

የአንበጣ መንጋ በታየባቸው አካባቢዎች፣ በባህላዊ ዘዴዎች የመከላከል ሥራ እየተሠራ እንደኾነ አቶ ገብረ ሕይወት ገልጸው፣ ይህንኑም የመከላከል ተግባር፣ ከፌዴራሉ መንግሥት እና ከአፋር ክልል ባለሞያዎች ጋራ በትብብር ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የአፅቢ ወረዳ ገብረኪዳን ቀበሌ፣ የአንበጣ መንጋው እንደታየና በአዝርዕት ላይ ጉዳት ስለማድረሱ ከተገለጸባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው፡፡

የቀበሌው ነዋሪ፣ አርሶ አደር ሓጎስ ገብረ እግዚአብሔር፣ በስልክ ለአሜሪካ ድምፅ እንደገለጹት፣ ሐምሌ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ወደ አካባቢያቸው የገባው የአንበጣ መንጋ፣ እርሳቸው የዘሩትን ማሽላ እና በሌሎችም አርሶ አደሮች ማሳ ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡

አርሶ አደር ሓጎስ፣ አካባቢያቸው ከአፋር ክልል ጋራ ወሰንተኛ እንደኾነ ገልጸው፣ አሁንም ተጨማሪ የአንበጣ መንጋ ስጋት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

በክልሉ ምሥራቃዊ ዞን ስቡሓሳዕሲዕ ወረዳ ወልዋሎ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት ሌላው አርሶ አደር ለገሰ ገብረ ሥላሴ በበኩላቸው፣ በአካባቢያቸው የአንበጣ መንጋ በተደጋጋሚ እየታየ እንደኾነ ገልጸው፣ መንጋው በእርሻ ማሳው ላይ እንዳያድር፣ በባህላዊ ዘዴዎች የማባረር ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

እስከ አሁን እንደ ክልል በሚካሔደው የመከላከል ሥራ፣ የኬሚካል ርጭት ጥቅም ላይ እንዳልዋለ፣ በክልሉ ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የዕፀዋት ጤና ክሊኒክ እና ተባይ መከላከል ቡድን መሪ፣ አቶ ገብረ ሕይወት ኀይለ ሥላሴ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ መንጋው የታየባቸው አካባቢዎች፣ በማር ምርታቸው የሚታወቁ እንደኾኑ የጠቀሱት ቡድን መሪው፣ የአንበጣውን መንጋ ለመከልከል ጥቅም ላይ የሚውለው ኬሚካል ደግሞ የምርቱን ዑደት እንደሚጎዳው አስረድተዋል፡፡

በቀጣይ፣ የአንበጣ መንጋው አሁን ከሚታይበት አብዝቶ ሊመጣ እንደሚችል የጠቆሙት አቶ ገብረ ሕይወት፣ ይህንኑ የተገነዘበ የመከላከል ዝግጅት እየተደረገ እንዳለ አስታውቀዋል። ሙሉ ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG